የኦሽዊትዝ ካምፕ ነፃ የወጣበት 81ኛ ክብረ በዓል ላይ 'ትውስታው ብርሃን ሊሆነን ይገባል’ መባሉ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቀድሞ የጀርመን ናዚ ማጎሪያ ካምፕ በነበረው ኦሽዊትዝ-ቢርኬናው ውስጥ በተከበረው ካምፑ ከተዘጋ 81ኛ ዓመት የመታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ተናጋሪዎች የመታሰቢያ በዓላቱ ዝም ብለው መደበኛ በዓላት ሆነው ተከብረው የሚያልፉ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባሻገር ትርጉም ያላቸው ሆነው መከበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ከማጎሪያ ካምፑ በህይወት የተረፉት በርናርድ ኦፌን እንደተናገሩት “ክስተቱን ማስታወስ ሸክም ሳይሆን፥ በጨለማ ውስጥ የሚመራን ብርሃን ሊሆንልን ይገባል” ያሉ ሲሆን፥ የኦሽዊትዝ ሙዚየም ዳይሬክተር የሆኑት ፒዮትር ሳይዊንስኪ በበኩላቸው ማስታወስ እና ልምድን እንደ “ሀብት” እና “ምልክት” ማየት ይገባል ብለዋል።
የመታሰቢያ ቀን
ከሰዓት በኋላ በተከበረው በዚህ የመታሰቢያ ቀን መርሃ ግብር ላይ ከማጎሪያ ካምፑ በህይወት የተረፉ ሰዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የዲፕሎማቲክ አካላት የተገኙ ሲሆን፥ የጠዋቱ መርሃ ግብር ላይ ወደ 20 የሚጠጉ የቀድሞ እስረኞች የካምፑ 81ኛ ዓመት የነፃነት ክብረ በዓልን አስመልክተው በቀድሞው ቁጥር አንድ ኦሽዊትዝ ካምፕ ውስጥ ‘የሞት ግድግዳ’ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ላይ የአበባ ጉንጉን እና ሻማዎችን ማኖራቸው ተነግሯል።
ስለ “መላእክቶቼ” የተሰጠ ምስክርነት
በቀድሞ የካምፑ ሕንፃ ውስጥ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ በዋናነት ንግግር ያደረጉት እ.አ.አ. በ1929 በክራኮው የተወለዱት እና ከሆሎኮስት ጥቃት በሕይወት የተረፉት በርናርድ ኦፌን ሲሆኑ፥ በርናርድ ባደረጉት ንግግር በጦርነቱ ምክንያት አስቸጋሪ የነበረውን የልጅነት ጊዜያቸውን፣ እናታቸው እና እህታቸው በበሽዊክ ካምፕ ውስጥ መገደላቸውን፣ እንዲሁም በኦሽዊትዝ ከአባታቸው ጋር የተለያዩበትን ክስተቶች ያስታወሱ ሲሆን፥ “አባቴ በግራ በኩል ወደ ሞት ተልኳል፥ እኔ ደግሞ ወደ ቀኝ በኩል ተላኩኝ፥ ያን ወቅት ለመጨረሻ ግዜ በዓይኖቻችን ስንተያይ አስታውሳለሁ፥ ለመጨረሻ ጊዜ እየተያየን እንዳለን ይሰማን ነበር” በማለት አስታውሰዋል።
“ከሞት የተረፍኩት ሌሎች ሰዎች ስለረዱኝ ነው፤ እነሱን ደግሞ መላእክቶቼ ብዬ እጠራቸዋለሁ” ያሉት በርናርድ፥ እነዚህን ሰዎች ሁሌ እንደሚያመሰግኑ ገልጸዋል።
በርናርድ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከኖሩ በኋላ ወደ ፖላንድ ለመመለስ መወሰናቸውን ጠቁመው፥ ስለ ክራኮው መኖሪያ ቤት እና ይህ ቤት እንደገና የደህንነት ስሜት ያገኙበት ቦታ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ “የበፊቱን ማስታወስ ሸክም ሳይሆን በጨለማ ውስጥ የሚመራን ብርሃን መሆን አለበት፥ እኛ ምስክሮች በቅርቡ ከዚህ ዓለም ድካም ልናርፍ እንችላለን፥ ነገር ግን ይህ ብርሃን ከእናንተ ጋር ይኖራል ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል።
ትውስታ እና ልምድ
የኦሽዊትዝ ሙዚየም ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ፒዮትር ሳይዊንስኪ በበኩላቸው በማስታወስ እና በተሞክሮ ላይ በማንፀባረቅ፥ እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ለዘመኑ ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ መንትያ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው በማለት የገለጹ ሲሆን፥ “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተገነባ ሥርዓት” እየተንኮታኮተ ባለበትና ዓለም አቀፍ ሕግም “በመጣስ” ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ትውስታን እንደ መጥፎ ሸክም ወይም እንደ መደበኛ ግዴታ ሊወሰድ እንደማይገባ ጠቁመዋል።
“ትውስታ ዳግም ሊተገበር የሚገባው ልምድ መወሰድ የለበትም፥ ነገር ግን እንደ እውነተኛ የድጋፍ ምንጭ እና የግንዛቤ እድገት መታየት ይገባዋል” ያሉት ዶክተር ሳይዊንስኪ፥ የማስታወስ መሠረት እና “ኃይል” የሚሆነው ከተረፉ ሰዎች ከሚገኝ ልምድ ነው ብለዋል።
የወንጀል እና የኃላፊነት ምንጮች
ኦሽዊትዝ “የፍፁም ሰብአዊነት መጓደል ምልክት” እና “በጀርመኖች የተደራጀ የሞት ፋብሪካ ነበር” ነበር ያሉት የፖላንድ ፕሬዝዳንት ካሮል ናውሮኪ፥ የሆሎኮስት ወንጀል እና ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ የፖላንድ ዜጎችን ጨምሮ የስድስት ሚሊዮን አይሁዶች ግድያ እ.አ.አ. ከ1930ዎቹ ጀምሮ የማህበራዊ ድጋፍ ያገኘው የአንድ የተወሰነ የጀርመን ግዛት ፖሊሲ ውጤት እንደሆነ አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እ.አ.አ. ከ1939 እስከ 1941 ባለው ጊዜ ውስጥ በፖላንዶች ላይ የተፈጸሙትን ጨምሮ ለዓመታት የዘለቀው ዓለም አቀፍ ግድየለሽነት እና የጅምላ ወንጀሎች ከጅምላ ጭፍጨፋው በፊት እንደነበረ ናውሮኪ አስታውሰዋል።
ጸጥታን በመቃወም
ለኦሽዊትዝ-ቢርኬናው ፋውንዴሽን ለጋሾችን በመወከል ንግግር ያደረጉት ዮሲ ማቲያስ ከህያው ትውስታ ወደ ታሪካዊ የትውስታ ሽግግርን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ የዓይን ምስክሮች ቁጥር እየተመናመነ መምጣቱን እና ከጥቃቱ የተረፉት ሰዎች የሚመሰክሩትን ነገር ማዳበር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፥ በዚህም ምክንያት “በጣም ወሳኝ ደረጃ ላይ እንገኛለን” ያሉ ሲሆን፥ እውነት ለትውልድ ተደራሽ እንድትሆን እና በመርሳት ወይም ታሪክን በመካድ እንዳይጠፋ የሆሎኮስት ምስክርነቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል።
የኦሽዊትዝ ነፃ መውጣት
እ.አ.አ. ጥር 27 ቀን 1945 በካምፑ ውስጥ የነበሩት ወደ 7,000 የሚጠጉ እስረኞች በቀይ ጦር ወታደሮች ነፃ የወጡበት ቀን ሲሆን፥ የጀርመን ናዚዎች በኦሽዊትዝ ካምፕ ፖላንዳውያን፣ ሮማዎች፣ የሶቪየት ጦር ምርኮኞች እና የሌላ ብሔር ተወላጆችን ጨምሮ በአብዛኛው አይሁዳውያን የሆኑ 1.1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን መግደላቸው ይታወቃል።
ዛሬ ላይ ኦሽዊትዝ የሆሎኮስት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግፍ ዓለም አቀፋዊ ምልክት ሆኖ የሚታይ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2005 የተባበሩት መንግስታት ጥር 27 ን ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ቀን አድርጎ መሰየሙ ይታወሳል።