ጀነራል አብዱልፈታ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችሉ የሽምግልና ዕድሎችን ውድቅ ማድረጋቸው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እሁድ ዕለት በአንካራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ህዝቡ በረሃብ፣ በመፈናቀል እና በጭካኔያዊ ድርጊቶች እየተሰቃየ ባለበት ወቅት ጦርነቱ ሊቆም የሚችለው የሚቆመው ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች እጅ ሲሰጡ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለማችን አስከፊው ሰብአዊ ቀውስ ተብሎ የተሰየመው በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በሱዳን ጦር ኃይል እና በኃይለኛው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መካከል በተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ ግልፅ ጦርነት መሸጋገሩ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ሀገሪቱ በጅምላ ግድያ እና አስገድዶ መድፈር እንዲሁም ብሔርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ስትናጥ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን፥ እስከ አሁን ድረስ በግጭቱ ከ40,000 በላይ ሰዎችን መሞታቸው ቢገለጽም፥ የእርዳታ ቡድኖች ግን ትክክለኛው ቁጥር እየተነገረ ካለው በብዙ እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ይናገራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የበሽታ ወረርሽኝ እና ረሃብ በመስፋፋቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው "የማይታሰብ" ስቃይ
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የጄኔራል አል-ቡርሃንን የቱርክ ጉብኝት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው “የማይታሰብ” ስቃይ ለማስቆም አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ነገር ግን ለረዥም ዓመታት ሱዳንን ሲመሩ የነበሩት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ስልጣን የያዙት የሱዳን ጦር ሰራዊት መሪ የሆኑት ጀነራል አብዱልፈታህ ጦርነቱ የሚያበቃው በሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ "ሄሜቲ" የሚመራው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይል እጅ ሲሰጥ ብቻ ነው በማለት ያሳሰቡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ጎረቤት ሀገራት ከግጭቱ እንዲርቁ በማስጠንቀቅ፥ መንግስታቸው ከአሁን በኋላ በሱዳን የሰላማዊ መፍትሄ አፈላላጊ ፍኖተ ካርታን የሚዘረዝረውን ዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን፣ ሳዑዲ አረቢያን እና ግብፅን ያቀፈውን የ “ኳድ” ተነሳሽነት ስልጣን እንደማይቀበል አስታውቋል።
ጀነራል አብዱልፈታ ሽምግልናውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የእርዳታ እጦትን እየተጋፈጠች ባለችበት እና ጦርነቱ እየተጠናከረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፥ በተለይም በሰሜን እና በደቡብ ኮርዶፋን እና በዳርፉር ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየሩ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል ተብሏል።
የሁለቱ ወገኖች ግጭት በነጭ አባይ ግዛት እና ከዋና ከተማው ካርቱም በስተደቡብ ያለውን አካባቢ እየጎዳ እንደሆነም ተነግሯል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመንን ጨምሮ ቁልፍ ለጋሾች ቀደም ሲል ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ተከትሎ የተከሰተው የሰብዓዊ ምላሹ ውድቀት የተባበሩት መንግስታት ለጎረጎሳዊያኑ ለ 2026 ዓ.ም. ያቀረበውን ጥሪ ከግማሽ በላይ በመቀነሱ ቀድሞውንም አስቸጋሪ የነበረውን የሃገሪቷን ሁኔታ ይበልጥ ያባብሰዋል ተብሏል።