ፈልግ

ሩሲያ በኦዴሳ ክልል ያደረሰችው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ተከትሎ ሩሲያ በኦዴሳ ክልል ያደረሰችው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት ተከትሎ 

ሩሲያ የገና በዓል እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዩክሬን ላይ የሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አደረሰች

የዩክሬን ባለስልጣናት እንደተናገሩት ሩስያ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳኤል ዩክሬን ላይ ባደረሰችው ጥቃት የአራት ዓመት ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጸው፥ ከዚህም ባሻገር የገና በዓል ሊከበር ሁለት ቀናት በቀሩበት እና ሀገሪቱ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ውስጥ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በተለያዩ ክልሎች የሃይል አቅርቦት መስመሮችን ማቋረጧ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በመላው ዩክሬን ያሉ ነዋሪዎችን ከሌሊት እንቅልፋቸው የቀሰቀሰው የሩሲያ ጥቃት የሃገሪቱ ባለስልጣናት እንደጠቆሙት በሳምንቱ ውስጥ ከተፈጸሙት የሩሲያ ጥቃቶች ከፍተኛው እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳሉት ሞስኮ ከ650 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ከ30 በላይ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ በከተሞች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ማነጣጠሯን አስረድተዋል።

በዚህ ጥቃት ቢያንስ ሶስት ሰዎች እንደተገደሉ እና ከእነዚህም ውስጥ በዋና ከተማዋ ኪየቭ አቅራቢያ አንዲት ሴት ህይወቷ ያለፈ ሲሆን፥ በሰሜን ምዕራብ ዢቶሚር ክልል አንድ ታዳጊ ሕፃን መገደሉን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

በ13 ክልሎች የሲቪል መሰረተ ልማቶች እና የኢነርጂ ተቋማት በመመታታቸው ምክንያት የሙቀት መጠኑ ከዜሮ ድግሪ ሴንቲግሬድ በታች በመውረዱ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አስከትሏል ሲሉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

የዩክሬን ወታደራዊ ሃይል እንደገለጸው የአየር መከላከያዎቹ አብዛኛዎቹን ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ማክሸፋቸውን ገልጸው፥ ነገር ግን በመኖሪያ ቤቶች፣ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አምኗል።

ዘለንስኪ ጥቃቱን አውግዘዋል
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከጥቃቱ በተጨማሪ ጥቃቱ የተፈጸመው ቤተሰቦች በሰላም ተገናኝተው አብረው ለማሳለፍ ተስፋ በሚያደርጉበት የገና ሰሞን በመሆኑ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ጊዜ ያወገዙ ሲሆን፥ ዘለንስኪ አክለውም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “መግደል ማቆም አለብን የሚለውን እውነታ መቀበል አንችልም” ብለው የተናገሩትን ንግግር አስታውሰዋል።

ጥቃቱ የተከሰተው በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር በተለያየ ጊዜ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ተወካዮች ጋር በማያሚ በተካሄደው የሰላም ድርድር ማግስት መሆኑ ተገልጿል።

በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው ባለ 28 ነጥብ የሰላም ስምምነት ዙሪያ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በታቀደው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ዩክሬን ሁለቱ ግዛቶቿን አሳልፋ እንድትሰጥ እንዲሁም የደህንነት ዋስትና እና የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕርዳታ ለማግኘት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅትን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት መተው እንደሚገባት የሚያሳስብ እንደሆነ ተገልጿል።

ትራምፕ በበኩላቸው በዩክሬን እና በሩሲያ መሪዎች መካከል ያለው ጥልቅ ግላዊ ጥላቻ ለአራት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማቆም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያወሳስበው ጠቁመዋል።

ትራምፕ ስለ ጥላቻ የተናገሩት 
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ  “እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን በተመለከተ እየታዩ ካሉት ችግሮች አንፃር በቁጥጥር ስር እንደሚሆን እና ምናልባትም ቀላልም ሊሆን እንደሚችል አስቤ ነበር” ካሉ በኋላ፥ “ነገር ግን በእነዚያ ሁለት ሰዎች (ዘለንስኪ እና ፑቲንን ማለታቸው ነው) መካከል ብዙ ጥላቻ አለ፥ ጥላቻ ሲኖር ደግሞ እንደሚታወቀው ጦርነት ይኖራል” ማለታቸው ይታወሳል።

ይህ የጠላትነት ስሜት በማክሰኞው ጥቃት ጎልቶ መታየቱ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም የኔቶ አባል ሀገራት ነገሮችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያዩ ማድረጉ ተገልጿል።

ፖላንድ በጥቃቱ ወቅት የአየር ክልሏን ለመጠበቅ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ዝግጁ ማድረጓን የገለጸች ሲሆን፥ ተጨማሪ ግጭቶች በሚጠበቁበት በአሁኑ ወቅት በጦርነት በምትታመሰው ዩክሬን የገና በዓል ሰላማዊ እንጂ ሌላ ነገር የተከሰተ አይመስልም ተብሏል።

24 Dec 2025, 14:15