የሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ ሰልፈኞች - በፊሊፒንስ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ ሰልፈኞች - በፊሊፒንስ   (AFP or licensors)

በሰብአዊ መብቶች ቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት መብቶች እየተጣሱ መሆኑ ተነገረ

በጎረጎሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 ላይ በሚከበረው የሰብአዊ መብቶች ቀን ላይ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት ኤጀንሲ በቀጣዩ ዓመት በ 133 ሃገራት ውስጥ ለሚገኙ 73 ሚሊዮን ሕፃናት ዕርዳታ ለማቅረብ እንዲቻል ባለድርሻ አካላት ሰብአዊ እርምጃዎችን እንዲወሰዱ ጥሪ ማቅረቡ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጎረጎሳዊያኑ ታኅሣሥ 10 ቀን የሚታሰበው የሰብአዊ መብቶች ቀን የተሰየመው በ 1948 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሁለንተናዊ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ያፀደቀበትን ቀን ለማሰብ እንደሆነ ይታወቃል።

ከ75 ዓመታት በፊት ታኅሣሥ 10 ላይ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰብዓዊ መብቶች ቀንን ማክበር የጀመረ ሲሆን፥ በወቅቱም የሰብዓዊ መብቶች ቀን መከበር ከመጀመሩ ከሁለት ዓመታት በፊት የፀደቀውን እና ‘ሁሉም ሰው እንደ ሰው ሊያገኘው የሚገባውን የማይገፈፉ መብቶችን ያቀፈውን’ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ በማስታወስ ተከብሯል።

ሆኖም ግን ከሦስት ሩብ ምዕተ-ዓመት በኋላ ዓለማችን አሁንም በፍትሕ መጓደል እና ሰብዓዊ ብዝበዛ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ተነግሯል።

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አራት ዓመታትን እያስቆጠረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት መርማሪዎች ጦርነቱ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሲቪሎች ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻልበት ደረጃ የሚደርስባቸውን ጥቃቶችን የሚገልጽ ሪፖርት ማውጣቱ ተገልጿል።

ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት በማንነታቸው ምክንያት ማሰቃየትን ጨምሮ እንግልት፣ የዘፈቀደ እስራት እና የግል ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸው ያለፍላጎታቸው ወደ አፍጋኒስታን የተመለሱ ግለሰቦችን ጉዳይ የሚያሳዩ ሰነዶችን ማውጣቱ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት - ዩኒሴፍ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት በጎረጎሳዊያኑ በ 2026 ዓ.ም. ከ200 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፥ በዚህም መሰረት ተቋሙ ‘የሰብዓዊ ድጋፍ እርምጃ ለህፃናት’ የሚል እንቅስቃሴ በማስጀመር፥ በሚቀጥለው ዓመት በ133 አገሮች ውስጥ ለ73 ሚሊዮን ሕፃናት ዕርዳታ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል።

በከፍተኛ ደረጃ የተፈጸሙ ከባድ ጥሰቶች
እየተገባደደ በሚገኘው የአውሮፓዊያኑ 2025 ዓመት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረጉ መርሃ ግብሮች ውስጥ 72 በመቶ የገንዘብ ድጋፍ ክፍተት በመታየቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገባቸው 20 ሃገራትን ችግር ውስጥ በመክተት 27 ሚሊዮን ሴቶች እና ሕፃናት የሆኑበትን 42 ሚሊዮን ሰዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ ያሉ የሰብአዊ ፍላጎቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው ዩኒሴፍ ለህጻናት ህይወት አድን አገልግሎት ወሳኝ የሆኑ የገንዘብ ድጋፎች እንዲደረጉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን የጠየቀ ሲሆን፥ በዚህም ጥሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 37 ሚሊዮን ልጃገረዶችን እና ከ9 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ለሚያካትተው 73 ሚሊዮን ህጻናትን ለማገዝ የሚውል 7.66 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መጠየቁ ተነግሯል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ህጻናት ‘በተደራራቢ ቀውሶች’ ውስጥ እንደሚኖሩ የገለጸው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ሪፖርት፥ በተለያዩ ሃገራት በሚከሰቱ ግጭቶች እና ጥቃቶች ምክንያት ህፃናት ከቤታቸው እንደሚሰደዱ እና ይህ ደግሞ ታይቶ ለማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ ጥሰቶች እንደሚያጋልጣቸው ይገልፃል።

በሰነድ የተመዘገቡ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች የፆታዊ ጥቃቶች ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በሄደበት በአሁኑ ወቅት ህፃናቱ በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች ሳይቀር ጥቃት እንደሚደርስባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በበርካታ ቀውሶች ውስጥ የተቸገሩትን እና ህፃናትን ለማግኘት የሚሞክሩ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ሆን ተብሎ ዒላማ እንደሚደረጉም ጭምር ሪፖርቱ ገልጿል።

መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እየተነፈጉ ወይም እየተጣሱ ነው
በዩኒሴፍ ግምት መሰረት በሚቀጥለው ዓመት ይህ አሃዝ እየጨመረ እንደሚሄድ እና የምግብ ዋስትና እጦት፣ የረሃብ አደጋ፣ የማያቋርጥ ብጥብጥ፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እና የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያጋልጡ ተገልጿል።

በየመን፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ፍልስጤም ወደ 8.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት በረሃብ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ እና ሌሎች12 ሚሊዮን የሚሆኑት ህፃናት ደግሞ በሶማሊያ፣ በናይጄሪያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሄይቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ማይናማር ተመሳሳይ ስጋት እንደተደቀነባቸው ተመላክቷል።

እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. ብቻ 41,470 የተረጋገጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው እና ይህም ካለፉት 20 ዓመታት በእጥፍ እንደሚበልጥ የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ በአፋጣኝ የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገ ከፆታዊ ጥቃት የተረፉ 360,000 የሚጠጉ ህፃናት እና እነሱን የሚንከባከቡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እና ድጋፍ ማግኘት እንደማይችሉ ገልጿል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል በዓለም ዙሪያ በግጭት፣ መፈናቀል እና በኢኮኖሚያዊ ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት ፈተናዎች እንዴት ተጠናክሮ እንደቀጠሉ በመግለጽ፥ የህፃናቱ ሕይወት የሚቀረፀው ብጥብጥ፣ የረሃብ ስጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአስፈላጊ መሰረተ ልማቶች መውደምን ከመሳሰሉ ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ችግሮች እንደሆነ አብራርተዋል።

እርዳታን መገደብ
እነዚህ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ባለው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ላይ በመጨመር የህፃናትን መሰረታዊ የሰብአዊ መብት የሆነውን ትምህርት የመማር መብትን እንደሚቀንሱ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በአውሮፓዊያኑ 2025 ዓመት ለጋሽ መንግስታት የዩኒሴፍ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን የመርዳት አቅምን የሚገድብ ድጋፍ የማቆም መመሪያዎች መውጣታቸውን በማስታወስ፥ ይህም በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ያለ ትምህርት፣ ጥበቃ እና ዋስትና የማጣት አደጋ የሚያጋልጠውን የ745 ሚሊዮን ዶላር ቅነሳን ጨምሮ ከባድ ውሳኔዎችን ማድረጉ ተመላክቷል።

ወይዘሮ ራስል እንደተናገሩት የገንዘብ ድጋፉ ከፍተኛ ቅነሳ የዩኒሴፍ ህይወት አድን ፕሮግራሞች አፈፃጸም ላይ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ ገልጸው፥ በዚህም የኤጀንሲው የፊት መስመር ሰራተኞች ለአንዳንድ አካባቢዎች ውስን አቅርቦቶችን እና አገልግሎቶችን ለተወሰኑት ብቻ ቅድሚያ መስጠትን ጨምሮ ህፃናት የሚያገኙትን ተከታታይ አገልግሎቶችን መቀነስን የመሳሰሉ አስቸጋሪ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ይገደዳሉ ብለዋል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተሯ ተቋማቸው አሁን ካለው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ችግር ጋር ለመላመድ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ህፃናት በበጀት ቅነሳው ምክንያት ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።

የሰዎች መሠረታዊ መብቶች ስጋት ላይ መውደቅ ከጀመሩ እና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከተጣሱ፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሕፃናት የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችልም ተገልጿል።

11 Dec 2025, 13:44