የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ተጨማሪ ግፍ ሊፈጸም እንደሚችል ማስጠንቀቁ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በነዳጅ ሀብት የበለጸገው ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ የሚደረገው ውጊያ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ አንስቶ የጅምላ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ አፈና እና ሰፊ ዝርፊያ እንደተፈጸሙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሄንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ሃላፊ ቮልከር ቱርክ እንደገለጹት በአካባቢው በሁለቱ ሃይላት መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እየተባባሰ በመምጣቱ ተጨማሪ የግፍ ተግባር ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ቮልከር ቱርክ በሱዳን ጦር ሃይሎች፣ በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች እና በሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ባለፈው ወር ብቻ ከ45,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ገልጸው፥ ለሲቪሎች ደህንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ እንዲኖር፣ ለእርዳታ ሰራተኞች ጥበቃ እንዲደረግ እና የመገናኛ አውታሮች መልሰው እንዲቋቋሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሱዳን ውስጥ የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ በፍጥነት እየተባባሰ እንደሆነ በማስጠንቀቅ፤ በአገሪቱ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ሱዳን ውስጥ ያለው አስከፊ ቀውስ... ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በኮርዶፋን እና በዙሪያው ያሉ አካባቢዎች የመከራ፣ የረሃብ፣ የሁከት እና የመፈናቀል ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
ከጥቅምት ወር መገባደጃ ጀምሮ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች በሰሜን ኮርዶፋን የምትገኘውን ባራ ከተማ ከተቆጣጠሩ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት በአከባቢው በተፈጸመ የአየር ድብደባ እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቢያንስ 269 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፥ ቮልከር ቱርክ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት በአከባቢው ያለው የኢንተርኔት እና የስልክ መቆራረጥ ችግር በስፍራው የተከሰተውን ነገር ሪፖርት ለማድረግ አዳጋች ስላደረገው ትክክለኛው የጉዳቱ መጠን እጅግ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጽህፈት ቤቱ ህፃናትን ጨምሮ የበቀል ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አፈና፣ ፆታዊ ጥቃት እና የግዳጅ ምልመላ መፈጸሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በርካታ ሲቪሎች ከተቀናቃኝ ቡድኖች ጋር ተባብረዋል በሚል ክስ መታሰራቸውን ሃላፊው ገልጸው፥ ከፋፋይ የሆኑ ንግግሮች ተጨማሪ ግጭቶችን ሊያስከስቱ ይችላሉ የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል።
“ባለፉት ወራት በአል ፋሸር ውስጥ ከተከሰቱት አሰቃቂ ድርጊቶች በኋላ ታሪክ እራሱን በመድገም በኮርዶፋን ሲደግም ማየት በእውነት በጣም አስደንጋጭ ነው” ያሉት ቮልከር፥ ኮርዶፋን ሌላ አል ፋሸር እንድትሆን መፍቀድ የለብንም ብለዋል።
በሦስቱ የኮርዶፋን ግዛቶች እጅግ አደገኛ የሆኑ ጥቃቶች ተባብሰው መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በሱዳን ሰሜናዊ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሱዳን ጦር ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ኤል ኦቤድ ከተማ አቅራቢያ በሐዘን ሥነ ሥርዓት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አብዛኛዎቹ ሴቶች የሆኑ ቢያንስ 45 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ህዳር 20 የሱዳን ጦር በደቡብ ኮርዶፋን፣ ካውዳ ከተማ ላይ ባደረሰው የአየር ጥቃት አብዛኛዎቹ ሲቪሎች የሆኑ ቢያንስ 48 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።