ተፈናቃይ ቤተሰብ ወደ ቶጎታ መንደር ሲሸሹ ተፈናቃይ ቤተሰብ ወደ ቶጎታ መንደር ሲሸሹ   (AFP or licensors)

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደቡባዊ ኪቩ ከ100,000 በላይ ህፃናት መፈናቀላቸው ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደቡባዊ ኪቩ ግዛት የኤም 23 አማፂያን እያደረሱት ባለው ጥቃት ምክንያት ህፃናት ለመሰደድ መገደዳቸውን አስጠንቅቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምስራቃዊ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት እየተባባሰ በመምጣቱ ከህዳር 22 ጀምሮ ከ100,000 በላይ ህፃናት መፈናቀላቸውን የገለጸው ዩኒሴፍ፥ በደቡባዊ ኪቩ ግዛት ውስጥ ያለው ግጭት በፍጥነት መባባሱ “በጣም አስጨናቂ” እንደሆነ ገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ ታኅሣሥ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ባደረጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል እንደገና በተቀሰቀሰው ጦርነት “ጥልቅ የሆነ ስጋት” እንዳላቸው ገልጸዋል።

ፈጣን የሆነ መፈናቀል
በደቡባዊ ኪቩ ውስጥ ብቻ ከህዳር 22 ጀምሮ ተባብሶ በቀጠለው ከባድ ጦርነት ከ100,000 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ500,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ዩኒሴፍ የገለጸ ሲሆን፥ በርካታ ቤተሰቦች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች መፈናቀላቸው እና በርካቶች ደግሞ ድንበር ተሻግረው ወደ ቡሩንዲ እና ሩዋንዳ መሰደዳቸውን አመላክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “ግጭቱ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር መፈናቀሉ የበለጠ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል” ሲል አስጠንቅቋል።

ከህዳር 23 ጀምሮ አራት ተማሪዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጎዳታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች ሕፃናትን በሚመለከቱ ጥሰቶች ስድስት ተማሪዎች መቁሰላቸው እና ቢያንስ በሰባት ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት በመድረሱ መማሪያ ክፍሎቻቸው በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የወደሙ መኖራቸው ተገልጿል።

ግጭቱን ሸሽተው ወደ ቡሩንዲ ከተሻገሩት መካከል ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 2 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ግማሽ ያህሉ ታዳጊ ህፃናት የሆኑበት ከ50,000 የሚበልጡ ሰዎች መሰደዳቸውን የገለጸው ዩኒሴፍ፥ ህፃናት በዚህ ግጭት በፍፁም ዋጋ መክፈል እንደሌለባቸው አሳስቧል።

የ ኤም 23 ግስጋሴ በደቡባዊ ኪቩ ቀጥሏል
በደቡባዊ ኪቩ የኤም 23 አማፂያን ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፥ የአይን እማኞች እንደገለጹት አማፂያኑ ባለፈው ሳምንት ከመንግስት ሃይሎች ይህ ነው የማይባል መከላከል ሳያጋጥማቸው ወደ ኡቪራ ከተማ ከገቡ በኋላ፥ የመንግስት ደጋፊ ከሆኑ የዋዛለንዶ ሚሊሻዎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት አድርገው የማኮቦላ ከተማን እና የካሴኬዚን መንደር መያዛቸው ተዘግቧል።

‘አክቿሊቴ’ የተባለው የኮንጎ ጋዜጣ ጠቅሰው የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በሩዋንዳ ይደገፋሉ ተብለው የሚነገርላቸው አማፂያኑ ከማኮቦላ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካሴኬዚ በሚገኘው ዋዛለንዶ ይዞታ ላይ ጥቃት ማድረጋቸውንና ምሽቱን እዚያው እንደቆዩ ተዘግቧል።

ክልላዊ ውጥረቶች
በቡሩንዲ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን ኡቪራ ከተማ መያዟ በቀጣናው ውጥረቱ እንዲባባስ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ሩዋንዳ ለኤም 23 ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ እንደማታደርግ በመግለጽ፥ ዳግም ለተቀሰቀሰው ግጭት የኮንጎ እና የብሩንዲ ወታደሮችን ተጠያቂ አድርጋለች።

ሆኖም ግን ቅዳሜ ዕለት በኤም 23 አማፂያን የደቡብ ኪቩ ገዥ ሆኖ የተሾመው ፓትሪክ ቡሱ ብዋ ንግዊ በአካባቢው የተሰማራው የብሩንዲ ጦር ሙሉ በሙሉ ‘ግዛቱን ለቆ በሰላም ወደ ሃገሩ መመለስ አለበት’ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ኤም 23 “በጦርነቱ ወቅት የተማረኩ በርካታ የብሩንዲ ወታደሮችን” ይዞ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፥ አማፂያኑ የያዛቸውን የብሩንዲ ወታደሮች “ወደ አገራቸው ሊመልሳቸው እንዳሰበ” ነገር ግን ቡሩንዲ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ይፋዊ ጥያቄ እንድታቀርብ መጠየቁ ተገልጿል።

የኮንጎ ፕሬዝዳንት አንጎላን መጎብኘታቸው
ሰኞ ዕለት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በማዕከላዊ አፍሪካ ቀጣናዊ ተግዳሮቶች ላይ ለመነጋገር እና የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር የአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ መግባታቸው ተነግሯል።

እንደ ራዲዮ ኦካፒ ዘገባ ከሆነ ምንም እንኳን በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት ህዳር 25 በዋሽንግተን ከተማ የተደረገው የሰላም ስምምነት ቢፀድቅም ግጭቱ በመቀጠሉ ምክንያት፥ ጉብኝቱ ያተኮረው በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ ያለመውን የሉዋንዳ የሰላም ሂደትን በመከለስ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ለወራት ያህል አንጎላ የአደራዳሪነት ሚናን ለኳታር እና ለዩናይትድ ስቴትስ ከማስረከቧ በፊት በተደራዳሪ ወገኖቹ መካከል በተደረገው ውይይት ላይ በሽምግልና አገልግላለች።

17 Dec 2025, 14:41