የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል  

የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በፕርዚዳንታዊ የጊዜ ገደብ ውዝግብ ውስጥ ብትገኝም ሃገራዊ ምርጫ ማካሄዷ ተነገረ

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ ያሉ ዜጎች ንትርክ በታየበት ምርጫ የፕሬዚዳንታዊ፣ የሕግ አውጪ፣ የክልል እና የማዘጋጃ ቤት ተወካዮችን መምረጣቸው የተነገረ ሲሆን፥ በሥልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዝዳንት ፋውስቲን-አርካንጅ ቱዋዴራን ጨምሮ ሰባት እጩዎች ለውድድር ቀርበዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፋውስቲን-አርቼንጅ ቱዋዴራ በሃገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የስልጣን ዘመናቸውን ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ ለማራዘም መወሰናቸውን ተከትሎ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መራጮች እሁድ ዕለት ፕሬዚዳንታዊ እና የህግ አውጪ እጩዎችን ለመምረጥ በውዝግብ የተሞላ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል።

ምርጫው የፕሬዝዳንቱን የስልጣን ዘመን ገደብ የሻረውን አጨቃጫቂ ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ የተቃዋሚ መሪዎች እና የሲቪል ማህበረሰቦች ሂደቱን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሲሉ ያወገዙ ሲሆን፥ አንዳንዶች ምርጫውን “የይስሙላ” በማለት ሙሉ በሙሉ ተቃውመዋል።

በመላ ሃገሪቱ ከ6,700 በሚበልጡ የምርጫ ጣቢያዎች 2.3 ሚሊዮን ሰዎች ለመምረጥ መመዝገባቸውን የብሔራዊ ምርጫ ባለስልጣን ያስታወቀ ሲሆን፥ የሃገሪቱ ዜጎች የፕሬዚዳንታዊ፣ የሕግ አውጪ፣ የክልል እና የማዘጋጃ ቤት ተወካዮችን መርጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎችን ልኳል
እንደ ሀገሪቱ ብሔራዊ የምርጫ ባለሥልጣን መግለጫ ከሆነ፣ ታዛቢዎቹ ከ"ግሬት ሌክስ" ክልል፣ ከመካከለኛው አፍሪካ መንግሥታት ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ እና ከአውሮፓ ሕብረት ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት የተውጣጡ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት ውጥረቱ የበረታበት እና በፖለቲካዊ እንቅፋት እየተወነጀለ ያለውን ምርጫ የሚከታተሉ 32 አባላትን የያዘ ልዩ የአፍሪካ ሕብረት የምልከታ ቡድን በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ መላኩ ተነግሯል።

የተቃዋሚዎቹ እጩዎች አኒስት-ጆርጅ ዶሎጉሌ እና የቀድሞ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ-ማሪ ዶንድራ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በክልላቸው የምርጫ ዘመቻ እንዳያደርጉ መከልከሉን በመግለጽ የከሰሱ ሲሆን፥ የፕሬዚዳንት ቱዋዴራ ቡድን ግን ክሱን ውድቅ አድርጓል።

እ.አ.አ. በ 2016 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣኑን የተረከቡት ቱዋዴራ ለረጅም ጊዜያት አለመረጋጋት ውስጥ በነበረችው ሀገር ላይ ስልጣናቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ የሚል ትችት የገጠማቸው ሲሆን፥ ሃገሪቷ ከፍተኛ የድፍድፍ ዘይት፣ ወርቅ እና ዩራኒየም ክምችት ቢኖራትም፥ እ.አ.አ. በ1960 ከፈረንሳይ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ለአስርት-ዓመታት በግጭት እና በደካማ አስተዳደር ስር የነበረችው መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ከአፍሪካ ድሃ ሀገራት አንዷ ሆናለች።

ከምርጫው በፊት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ማዕከላዊ አፍሪካውያን በሰላማዊ መንገድ ድምጽ እንዲሰጡ ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ጉተሬዝ የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ሂደቱ ‘ሰላማዊ፣ ሥርዓታማ፣ አካታች እና ተዓማኒነት ያለው’ መሆኑን እንዲያረጋግጡ በመጠየቅ፥ የፖለቲካ ተዋናዮች ግጭትን የሚቀሰቅሱ ወይም የህዝብ አመኔታን የሚሸረሽሩ ተግባራትን እንዲያስወግዱም ተማጽነዋል።

29 Dec 2025, 14:53