ጋዛ ከሁለት ዓመታት ውድመት በኋላ ለማገገም ዓመታትን እንደሚፈጅባት ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከሁለት ዓመታት ጦርነት በኋላ ጥቅምት ወር ላይ የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት ግጭቱ ለአፍታ ቆም እንዲል ቢያደርግም፥ ነገር ግን አሁንም ድረስ በጋዛ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ ነው ተብሏል።
በአከባቢው የሚታየው ውድመት እና መፈናቀል በጣም አስደንጋጭ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ አሁንም ድረስ ቤተሰቦች በድንኳን እና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ሰዎች በተዘጋጁ መጠለያዎች ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ገልፆ፥ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የሆነ መኖሪያ ቤት አስፈላጊነትን በአጽንዖት አስጠንቅቋል።
በአከባቢው የምግብ ዋስትና እጦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፥ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይፋ እንዳደረገው አብዛኛው አባወራዎች መሠረታዊ የሆኑ ምግቦችን የመግዛት አቅም እንደሌላቸው እና ዕለታዊ ፍጆታ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ደረጃ በታች መሆኑን ጠቁሟል።
በቀጠናው ረሃብ መከሰቱ ከታወቀበት ነሃሴ ወር ጀምሮ የተሻሻሉ የምግብ አቅርቦቶች ቢኖርም፥ አሁንም ድረስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ‘የአስቸኳይ ጊዜ’ የረሃብ ደረጃ ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከ100,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በ“አደጋ” ውስጥ እንደሚኖሩ እና በከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ደረጃ ውስጥ መመደባቸው ተገልጿል።
በቀጠናው ከሚታየው አፋጣኝ ፍላጎቶች ባሻገር የጥፋት መጠኑ አስደንጋጭ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በተባበሩት መንግስታት የሳተላይት ትንታኔ መሰረት ጥቅምት ወር ላይ በተደረገው ምልከታ 81 በመቶው የጋዛ መዋቅሮች መጎዳታቸውን እና ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን አመላክቶ፥ የመልሶ ግንባታው መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው የጋዛ የድህረ ጦርነት መልሶ ግንባታ ጥረት በቅርብ ጊዜ በተገመቱት ግምቶች መሰረት ወጪው ከ 70 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያወጣ በማስታወስ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ትልቁ የመልሶ ግንባታ ወጪ ሊሆን እንደሚችል የጠቆመ ሲሆን፥ ይህንንም ለማከናወን አስርት ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።