የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአንድ ዓመት ውስጥ 50,000 ሴቶች መገደላቸውን ይፋ አደረገ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እህት አቢ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ አደገኛ የጥፋት ማዕከል ከሆነችው የሱዳኗ ኤል ፋሸር ከተማ ሆነው መረጃ የሚሰጧቸው ሴቶች ረሃብ፣ መፈናቀል፣ መደፈር እና የቦምብ ድብደባዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን እንደሚነግሯቸው ገልጸው፥ በተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ጂኔቭራ አና ሙታቫቲ በበኩላቸው በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከ500 ቀናት በላይ በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) ከበባ ስር የነበረው ይህ አከባቢ የጅምላ ግድያ እና ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጸው፥ በተለይ ሴቶች ለከባድ መከራዎች መጋለጣቸውን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፋዊ አሃዞች ጥቃቶች መስፋፋታቸውን ያሳያሉ
ስጋቱ ግን በጦርነት አውድ ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፥ እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምት መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ 840 ሚሊዮን ሴቶች ከሦስቱ በአንዷ ላይ በሥራ ባልደረባ ወይም በሌላ ሰው አካላዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው፣ ወይም ሁለቱም ጥቃቶች በሕይወታቸው ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንደሚደርስባቸው ገልፆ፥ ይህ አሃዝ ህዳር 16 የተከበረውን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የማስወገድ ዓለም አቀፍ ቀንን አስፈላጊነት እንደሚያጎላ አመላክቷል።
በየአስር ደቂቃው አንዲት ሴት በዓለም ውስጥ በሆነ ቦታ ላይ እንደምትገደል የሚያሳየው አዲስ የወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት በጣም አሳዛኝ ከሆኑ እውነታዎች ውስጥ አንዱን አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ በሪፖርቱ መሰረት ባለፈው ዓመት ወደ 50,000 የሚጠጉ ሴቶች የግድያ ሰለባዎች ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ 60 በመቶዎቹ የተገደሉት በአጋሮች ወይም በዘመድ መሆኑ ተገልጿል። በንጽጽር በወንዶች ግድያ ሰለባ ከሆኑት መካከል 11 በመቶው ብቻ በቤተሰብ አባላት መገደላቸውን እና የሥርዓተ-ፆታ አለመመጣጠን እና የሴቶች ጥላቻ ቁልፍ ምክንያቶች መሆናቸውም ጭምር ተገልጿል።
በ 2015 ዓ.ም. ከነበረው በመጠኑ ያነሰ ቢሆንም በአማካይ በየቀኑ 137 ሴቶች እንደሚገደሉ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ቁጥር በተለያዩ ሀገራት በሚወጡ ሚዛናዊ ያልሆኑ ሪፖርቶች ተጽዕኖ እንደሚደረግበት እና አፍሪካ ባለፈው ዓመት 22,000 ገደማ ተጠቂዎች የነበሩባት ቢሆንም በዚህ ዓመት ከፍተኛውን ቁጥር ማስመዝገቧ ተገልጿል።
የ ‘ኦን ላይን’ ጥቃት መስፋፋቱን ቀጥሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቴክኖሎጂ እድገት ለአዳዲስ ጥቃቶች አስተዋፅዖ ማድረጉን በመጠቆም፥ እነዚህም ምስሎችን እና መረጃዎችን ያለ ፍቃድ ማጋራት፣ የሰውን የግል ጉዳይ ማሰስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የተፈጠሩ ጥልቅ የውሸት ቪዲዮዎችን እንደሚያካትቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ፆታዊ ትንኮሳ እና የተቀናጀ የጥላቻ ዘመቻዎች በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ እንደሆነም ተመላክቷል።
ከ38 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴቶች በ ‘ኦን ላይን’ ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚገመት ሲሆን፥ 85 በመቶው ደግሞ በሌሎች ሴቶች ላይ በዲጂታል መድረኮች የሚደርስ ጥቃትን እንደሚያካትት ተነግሯል።
የታሊታ ኩም ቁርጠኝነት
“በተለይ በዚህ ቀን ግንዛቤን ማሳደግ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው” ያሉት በገዳማዊያት የሚመራው ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የሚሰራው የታሊታ ኩም ትስስር ዓለም አቀፍ አስተባባሪ የሆኑት እህት አቢ አቬሊኖ፥ የዲጂታል ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን እና የኦን ላይን ዓለም በአሁኑ ወቅት ዋነኛው የብዝበዛ ቦታ መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነት እና ግጭት በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት ላይ ያለውን ተጽእኖ ለማሰላሰል የታሊታ ኩም አባላት በዛሬው ዕለት በድህረ ገጽ መሰባሰባቸውን የጠቆሙት ሲስተር አቢ፥ በተለይ በዩክሬን፣ በደቡቡ ንፍቀ ዓለም፣ በአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በኢስያ የሚገኙ ተጋላጭ በሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ትኩረት አድርገናል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ አውሮፓ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተገደው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሴቶችን መቀበሉን እንደቀጠለች ገልጸዋል።
47,000 ሰለባዎችን እና በሕይወት የተረፉ ሰዎችን መድረስ
እህት አቢ ከቅርብ ጊዜ ታሪኮች መካከል እርዳታ የጠየቀችውን የደቡብ ሱዳን ወጣት ሴት ጉዳይ በማስታወስ፥ ወጣቷ የት እንዳለች ባያውቁም የትስስሩ አባላት ሊያገኟት እንደቻሉ እና በጣሊያን ውስጥ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በመተባበር ሴትየዋ ወደ ቻድ ተወስዳ እንደነበር፣ ብሎም እራሷም የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ከነበረችው እናቷ ጋር እንደገና መገናኘት እንደቻለች አስረድተዋል።
በታሊታ ኩም የቅርብ ጊዜ ሪፖርት መሠረት ትስስሩ በ 2017 ዓ.ም. ብቻ 47,000 ተጎጂዎችን እና በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ማገዙ የተገለጸ ሲሆን፥ እህት አቢ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ሃሳባቸው ዛሬ ላይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከተጠቁ ሴቶች እና ልጃገረዶች ጋር እንደሆነ ጠቁመው፥ እንደ ታሊታ ኩም ማዳመጥን፣ ጥበቃን እና ርህራሄን በመስጠት፥ እያንዳንዷ ልጃገረድ ተስፋን፣ ደህንነትን እና እንደገና ለመጀመር ጥንካሬን እንድታገኝ ከተሰቃዩት ጋር ለመቀራረብ ቃል ኪዳናችንን እናድሳለን ብለዋል።