ናይጄሪያ ውስጥ ከሚገኝ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ከ300 በላይ ተማሪዎች መታገታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በናይጄሪያ አግዋራ አውራጃ በሚገኘው የቅድስት ማርያም የካቶሊክ ትምህርት ቤት ጭምብል የለበሱ ታጣቂዎች ቅጥር ጊቢውን በሞተር ሳይክሎችና በከባድ መኪናዎች ከወረሩ በኋላ ከ300 በላይ ተማሪዎችን እና መምህራንን በግዳጅ አግተው መውሰዳቸው ተገልጿል።
በምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኘው ኒጀር ግዛት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ኮማንዶዎች በፈፀሙት አሳዛኝ የጅምላ አፈና ከ 300 በላይ ተማሪዎች ታግተው መወሰዳቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ትዕይንት የተከሰተው በኬቢ ግዛት 25 ሴት ተማሪዎች ታፍነው ከተወሰዱ ከአንድ ሳምንት በኋላ፥ እንዲሁም ህዳር 9 በምዕራብ ቋራ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የኢሩኩ ቤተክርስትያን ላይ ከደረሰ ጥቃት በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
እስካሁን ድረስ ለዚህ በሌሊት ለተፈፀመው ድርጊት ኃላፊነቱን የወሰደ ወይም የቤዛ ጥያቄ ያቀረበ ቡድን አለመኖሩ የተነገረ ሲሆን፥ ነገር ግን ከጀርባው የቦኮ ሃራም አሸባሪዎች መኖራቸው እየተገለጸ ይገኛል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምላሽ
በወሩ መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ እየተፈጸሙ ያሉትን የተለያዩ ጥቃቶች “በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም ጥቃት” በማለት የገለጹ ሲሆን፥ በናይጄሪያ ፈጣን ወታደራዊ ጣልቃገብነት እንደሚኖር በማስጠንቀቅ፥ ናይጄሪያ ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ እንደምትገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ፕረዚዳንት ትራምፕ እነዚህ የሽብር ድርጊቶች ካልቆሙ ለናይጄሪያ የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ በአስቸኳይ እንደሚያቋርጡ ቢገልጹም፥ ነገር ግን የናይጄሪያ መንግስት በሀገሪቱ ያሉ ክርስቲያኖች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚለውን ክስ በማስተባበል፥ ይልቁንስ ጥቃቱ የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር በሁሉም ናይጄሪያውያን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ ገልጿል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ጆናታን ፕራት በበኩላቸው ናይጄሪያ በሀገሪቱ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንድታስቆም ግፊት ለማድረግ ዋሽንግተን በፔንታጎን እርዳታ በናይጄሪያ ማዕቀብ ለመጣል እና የፀረ-ሽብርተኝነት እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበች መሆኑን ገልጸዋል።
ፕራት ይህ እቅድ የሀይማኖት ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ማዕቀብን እና የጦርነት ዲፓርትመንት በፀረ-ሽብርተኝነት ላይ መሳተፍን እንደሚያጠቃልል ጠቁመው፥ ዋሽንግተን በተለይም ለናይጄሪያ መንግስት የሚሰጠውን የደህንነት ድጋፍ እና እንዴት ሀብቶችን እንደሚጠቀም እንዲሁም የመረጃ እና የመረጃ ልውውጥን እየገመገመች መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገረ ስብከቱ የተላለፈ ውግዘት
የኒጀር ግዛት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቡበከር ኡስማን ‘በአግዋራ አውራጃ በሚገኘው የቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በመታገታቸው ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው’ በመግለጽ፥ ታግተው የተወሰዱት ሰዎች ቁጥር እስካሁን በግልጽ እንዳልቀረበ የተናገሩ ሲሆን፥ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የአካባቢው መንግስት ለጥንቃቄ ሲባል ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማዘዙን አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።
አቶ ኡስማን በማከልም “እንደ አለመታደል ሆኖ የቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት ለባለሥልጣናት ሳያሳውቅ ተማሪዎችን እና ሰራተኞችን ሊወገድ ለሚችል አደጋ በማጋለጥ የትምህርት እንቅስቃሴውን ቀጥሏል” ሲሉ ትምህርት ቤቱን ወቅሰዋል።
የኮንታጎራ ሀገረ ስብከት የቫቲካን ዜና ወኪል ለሆነው ፊደስ በላከው መግለጫ የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ ጃታው ሉካ ጆሴፍ በጥቃቱ አንድ የጸጥታ አባል በጽኑ ቆስሎ እንደነበር እና ይህ ጥቃት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መድረሱን ገልጸው፥ “የኮንታጎራ ሀገረ ስብከት ጥቃቱን አጥብቆ እንደሚያወግዝ፣ ለታገቱት ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው ደህንነት እጅግ እንደሚያሳስበው እና የጸጥታ አካላት መረጃው በአስቸኳይ እንደተነገራቸው እና ታጋቾቹ በሰላም እንዲመለሱ የተቀናጀ ጥረቶችን መጀመራቸውን” በመግለጫው ገልጸዋል።
የጂሃዲስቶች አመፅ
በናይጄሪያ በጅምላ የሚፈፀሙ አፈናዎች በብዛት እየታዩ የሚገኙ ሲሆን፥ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ስፍራ ላይ የምትገኘው እና በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው ናይጄሪያ በመካከለኛው እና በሰሜን-ምዕራብ የአገሪቱ ግዛቶች የሚፈጸሙት ጥቃቶች ብዙውን ጊዜ ባለስልጣናት በአጠቃላይ “ሽፍቶች” ብለው በሚጠሩት ወንጀለኛ ቡድኖች እንደሚፈጸሙ ይገልፃሉ።
ሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍልም ለሃያ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጂሃዲስት አማጽያን በርካታ ጥቃቶች እንደሚደርስበት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው እነዚህ ጥቃቶች ለ40,000 ሰዎች ሞት እና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።