ፈልግ

ህዝቡ የምግብ እርዳታ ለማግኘት በሚታገልበት ወቅት እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው የአየር ላይ ጥቃት መቀጠሉ ተገልጿል ህዝቡ የምግብ እርዳታ ለማግኘት በሚታገልበት ወቅት እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው የአየር ላይ ጥቃት መቀጠሉ ተገልጿል   (AFP or licensors)

የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ንግግር በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የእስራኤል የአየር ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነገረ

በቅርቡ የሰላም ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል የሚል ተስፋ እያደገ በመጣበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የአየር ድብደባ እንደቀጠለች ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ ቅዳሜ ማለዳ ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደተናገሩት በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የቀሩት ታጋቾች በሙሉ ይለቀቃሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የታጋቾችን መፈታት እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመው የድርድር ሂደት ላይ ተስፋ እየተጣለ ባለበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል ጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ መቀጠሏ የተገለጸ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቅዳሜ ማለዳ ላይ እንደተናገሩት በጋዛ የታገቱ ዜጎች መለቀቃቸውን "በመጪዎቹ ቀናት" አሳውቃለሁ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ “ሐማስ ትጥቁን ይፈታል እንዲሁም ጋዛ በቀላልም ሆነ በከባድ መንገድ ከወታደራዊ ኃይል ነጻ ትሆናለች፤ ደግሞም ይሳካል” ያሉ ሲሆን፥ ሐማስ በበኩሉ ባለፈው አርብ በአሜሪካ የሰላም ዕቅድ መሠረት እስራኤል ፍልስጤማዊያን እስረኞችን ከለቀቀች እና የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገች በበኩሉ ታጋቾችን ለመልቀቅ መስማማቱ ይታወሳል።

ሆኖም ግን ቡድኑ ትጥቅ መፍታትን በሚመለከት የገለጸው ነገር የሌለ ሲሆን፥ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መደራደር እንደሚፈልግ ጭምርም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ሐማስ ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባ ማካሄዷን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ‘እልቂት’ መፈጸሟን እንደቀጠለች መሆኗን ገልጾ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግባት አሳስቧል።

የአሜሪካ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ጦርነቱ ባስቸኳይ እንዲቆም እና በሐማስ ስር ያሉ 20 ታጋቾች፣ እንዲሁም ሞተዋል የተባሉትን ጨምሮ እንዲለቀቁ ሃሳብ የሚያቀርብ ሲሆን፥ የሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎች በሚቀጥሉት ቀናት በግብፅ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሟቾች ቁጥር ከ67,000 በልጧል
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቀው ጦርነቱ ከጀመረበት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ67,000 በላይ መድረሱን ገልጾ፥ በዚህም መሰረት 67,074 ሰዎች መሞታቸውን እና 169,430 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል። ባለሥልጣናቱ በሰጡት መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ሁለት ሕፃናት በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሞታቸውን ገልጸው፣ በአጠቃላይ በምግብ እጥረት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 154 ሕፃናትን ጨምሮ 459 መድረሱን ገልጸዋል።

የሁቲ ጥቃት
በሌላ ዜና የእስራኤል አየር መከላከያ ዘዴዎች እሁድ ማለዳ በየመን የሁቲ ሃይሎች የተተኮሰውን ባለስቲክ ሚሳኤል እንደጣሉ የተነገረ ሲሆን፥ የታጣቂዎቹን ሚሳኤል ተከትሎ በቤን ጉሪዮን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በሙት ባህር እና በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ በርካታ ሰፈራዎች ላይ የአየር ጥቃት ማንቂያ ሳይረኖችን መሰማታቸው እና በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ወደ መጠለያ እንዲገቡ ማድረጉ ቢነገርም፥ በሰው ህይወት ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ ተገልጿል።

ሁቲዎች ከ10 ዓመታት በፊት በየመን ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘውን መንግሥት ካባረሩ እና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲፈጠር ካደረጉ በኋላ አብዛኛውን የሃገሪቱን የሰሜን ምዕራብ አከባቢዎች ተቆጣጥረዋል።

ሁቲዎች ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ የጋዛ ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በእስራኤል እና በቀይ ባህር በሚገኙ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ የሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፥ እስራኤል በየመን የሁቲ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት እንደምትፈጽም ይታወቃል።

06 Oct 2025, 16:36