እስራኤል ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ያደረሰችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ - የማህደር ምስል እስራኤል ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ያደረሰችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ - የማህደር ምስል  

የተ. መ. ድ. ዋና ጸሃፊ በቅድስት ሀገር ውስጥ ያሉ የግጭት ዑደቶች 'መቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ' ሊደርስ እንደሚችል አስጠነቀቁ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ በጋዛ ውስጥ ያለማቋረጥ እየተከሰተ ያለው ችግር 'መቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ' እየተቃረበ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ብቸኛው መፍትሄ ተብሎ የቀረበው የእስራኤል እና የፍልስጤም የሁለት-ሃገራት መፍትሄ በፈረንሳይ እና በሳውዲ አረቢያ የሚመራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲሆን፥ ዋና ጸሃፊው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን ለመፍታት የሁለት ሉአላዊ ሃገራት መፍትሄ ወደ ማክተሙ እየተቃረበ መምጣቱን ጠቁመው፥ ለዚህም ምክንያት ያሉት የእስራኤል ሰፈራ እየተስፋፋ መሄዱን፣ በግዳጅ መፈናቀል እና ፍፁም ተስፋፊነት በመበራከቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅድስት ሀገር እየተፈጸመ ያለው የአደገኛ ጥቃት ዑደቶች 'መቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ' ሊደርሱ እንደሚችሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ በአክራሪ ሰፋሪዎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ጨምሮ የጥቃት ዑደቶቹ ሕገ-ወጥ የእስራኤልን ወረራን በማጠናከር ክልሉን ሊወጣው ወደማይችልበት ደረጃ እንዲቃረብ ማድረጉን ጉቴሬዝ ተናግረዋል።

እስራኤል ኢ1 (E1) በተሰኘው አካባቢ የምታካሄደውን የሰፈራ ግንባታ ማፅደቋን ያወገዙት ሃላፊው፥ ይህ ተግባር ዌስት ባንክን እንደሚገነጠል እና የወደፊቱን የፍልስጤም ግዛት ሉዓላዊነት እንደሚያሰጋ አስጠንቅቀው፥ የእስራኤል ሰፈራ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ህግን በግልፅ መጣስ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጉቴሬዝ ፈረንሳይን እና ሳውዲ አረቢያን በሁለት ሀገራት የመፍትሄ ሃሳብ ላይ የተካሄደውን ከፍተኛ ጉባኤ ማነቃቃታቸውን እና የተለያዩ ሃገራት ለፍልስጤም ሃገርነት እውቅና መስጠታቸውን አወድሰዋል።

ጉተሬዝ ለጋዛ የተሻለ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲባል የዘር ማጽዳት ተግባርን በመቃወም እና ወደ ሀገርነት የሚደረገውን ግልጽ መንገድ በማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ህግ ላይ የተመሰረተ ማዕቀፍ እንዲኖር ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የሰፋሪዎች ጥቃት እንዲቆም፣ የተስፋፊነት ተግባራት እንዲገታ እና እስራኤል የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እንድታከብር አሳስበዋል።

“ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም በግጭት አይገነባም” ያሉት ጉቴሬዝ፥ ችግሩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ፣ የዓለም አቀፍ ህግ እንዲከበር እና አጠቃላይ የሰው ልጅ ክብር እንዲጠበቅ የጋራ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አዲስ የጋዛ የሰላም ዕቅድን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቁ ሲሆን፥ የሁለቱ መሪዎች ዕቅድ፤ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በአፋጣኝ እንዲቆሙ እንዲሁም ሐማስ በ72 ሰዓታት ውስጥ 20 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና የሞቱ ታጋቾችን አስክሬን እንዲያስረክብ ምክረ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፥ በምላሹም በመቶዎች የሚቆጠሩ የታገቱ የጋዛ ነዋሪዎች የሚለቀቁ ይሆናል ተብሏል።

መሪዎቹ በዋይት ሀውስ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ ትራምፕ "ለሰላም ታሪካዊ ቀን" ሲሉ ዕቅዱን ያሞካሹ ሲሆን፥ ሐማስ በሰላም ዕቅዱ የማይስማማ ከሆነ ኔታንያሁ "የጀመሩትን ሐማስን የማጥፋት ዘመቻ" አሜሪካ እንደምትደግፍ አሳስበዋል።

ኔታንያሁ በበኩላቸው ሐማስ ዕቅዱን ካልተቀበለ ወይም ካልተገበረ እስራኤል "የጀመረችውን ትጨርሳለች" ሲሉ መዛታቸው ተገልጿል።

30 Sep 2025, 15:02