ፈልግ

አንዲት ፍልስጤማዊት ሴት በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በምትገኘው ኑሴራት ከአሸዋ ውስጥ እህል ስትፈልግ አንዲት ፍልስጤማዊት ሴት በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በምትገኘው ኑሴራት ከአሸዋ ውስጥ እህል ስትፈልግ   (AFP or licensors)

በጋዛ በረሃብ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 197 መድረሱ ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በጋዛ በረሃብ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ፥ በአከባቢው ከዚህ የሚብስ አስከፊ ሁኔታን ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዋና ኃላፊ ሲንዲ ማኬይን በጋዛ ሰርጥ በአሁኑ ወቅት 500,000 ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠው ባሉበት ሁኔታ ጥቂት ከአየር ላይ የሚጣሉ የእርዳታ ምግቦች ትክክለኛ መፍትሄ አይደሉም ሲሉ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በጋዛ በረሃብ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 197 ከፍ ማለቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አራት ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸውን እና ከሟቾቹ መካከል ግማሽ ያህሉ ህጻናት መሆናቸውን የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ይህ አሃዝ የወጣው በአከባቢው እየተባባሰ የመጣው የረሃብ ቀውስ ምክንያት ዓለም አቀፋዊ ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ ተቋም (IPC) በአብዛኛው የጋዛ አከባቢዎች የረሃብ ሁኔታዎች መስፋፋታቸውን በመጠቆም፣ ከዚህ የባሰ አስከፊ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ወደ 6,000 የሚጠጉ የጭነት መኪኖች ድንበር ላይ የሰብዓዊ እርዳታ ምግቦችን ጭነው ወደ ጋዛ ለመግባት ፍቃድ እየተጠባበቁ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን፥ ባለፈው ሳምንት እስራኤል ወደ ጋዛ ምግብ ከአየር ላይ እንዲጣል ፈቅዳ የነበረ ቢሆንም፥ ነገር ግን የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት እርምጃው በቂ እንዳልሆነ እና በአብዛኛው ማስመሰያ ነው ሲሉ ተችተዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ሚሮስላቭ ጄንካ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደራዊ ዘመቻዎችን በመላው የጋዛ ሰርጥ ሊያስፋፉ ይችላል ተብሎ የወጡትን ዘገባዎች በማስታወስ ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ ተጨማሪ ስቃይ እና የህይወት መጥፋትን ለመከላከል እስራኤል የሰብአዊ እርዳታን በአስቸኳይ እና ያለ እገዳ መፍቀድ እንዳለባት አሳስበዋል።

08 Aug 2025, 15:24