ፈልግ

የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት   (AFP or licensors)

የአውሮፓ መሪዎች ዩክሬን የምትሳተፍበት የሰላም ጉባኤ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የአውሮፓ መሪዎች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በታቀደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዩክሬንን እንዲያሳትፉ ጥሪ አቀረቡ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጪው አርብ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሚያደርጉት ውይይት ዩክሬንን እንዲያሳትፉ የአውሮፓ መሪዎች የጠየቁ ሲሆን፥ የጀርመኑ መራሄ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝ ሁለቱ መሪዎች በአላስካ በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪም እንደሚሳተፉ ያላቸውን ተስፋ እና ግምት ተናግረዋል።

ሜርዝ ለጀርመን መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት በርሊን ዜሌንስኪ በንግግሩ ላይ መገኘታቸውን ለማረጋገጥ ከዋሽንግተን ጋር በቅርበት እየሰራች እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ሃላፊ ካጃ ካላስ በበኩላቸው “በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ዩክሬንን እና የአውሮፓ ህብረትን ማካተት እንዳለበት፥ ምክንያቱንም ጉዳዩ የዩክሬን እና የመላው አውሮፓ ደህንነት ጉዳይ ነው” በማለት ይህንኑ ሀሳብ አስተጋብተዋል።

ትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል "አንዳንድ የመሬት ልውውጦች" ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆሙ ሲሆን፥ ሩሲያ የትኛውን የዩክሬን ግዛት ልትወስድ እንደምትችል ባይታወቅም "የመሬት ልውውጥ" የሚለውን ሐረግ ሲጠቀሙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ትራምፕ ከአርብ ዕለቱ ውይይት በኋላ ወደፊት የሚካሄደው ስብሰባ ዜሌንስኪን ሊያካትት እንደሚችል እና ፑቲንን እና ራሳቸውን ጨምሮ የሦስትዮሽ ውይይት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል በ50 ቀናት ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ ካልተቻለ ሩሲያ ላይ "ከባድ" ማዕቀብ እንደሚጥሉ ከዛቱ ከቀናት በኋላ ዜሌንስኪ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ ውይይት እንዲደረግ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እሁድ ዕለት አፅንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር ዓላማ የዩክሬይን እና የሩሲያ መሪዎችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት እንደሆነ ገልጸው፥ ቭላዲሚር ፑቲን ከዩክሬኑ መሪ ዜሌንስኪ ጋር በጭራሽ እንደማይቀመጡ መናገራቸውን ገልጸዋል። 

ጄዲ ቫንስ አክለውም በመሠረቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ በመሃላቸው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማስገደድ ያለባቸው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኪየቭ እውቅና ሳይኖራቸው በሚያደርጉት ስምምነት ላይ ስጋት እንዳለ እየተገለጸ ይገኛል።

የትራምፕ የቀድሞ የደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን አርብ ዕለት የሚካሄደው የትራምፕ-ፑቲን ስብሰባ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪን ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚያስገባቸው አመላክተው፥ “እኔ እንደማስበው ትራምፕ የፑቲንን እቅድ አስቀድሞ በማወቅ፣ በጣም ሊመቻቸው በሚችል አንድ ነገር ላይ ዜሌንስኪን ለማስገደድ የታሰበ ሊሆን ይችላል” ያሉ ሲሆን፥ ቦልተን አክለውም ከዚህ ንግግር በኋላ ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ትራምፕ ከዜሌንስኪ ጋር በኦቫል ቤተመንግስት ውስጥ የነበራቸው አስከፊ ቆይታ አሁንም ሊደገም እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቀደም ብለው ዩክሬናውያን “መሬታቸውን ለወራሪዎች እንደማይሰጡ” ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ ዩክሬንን ያላሳተፈ የትኛውም የመፍትሄ ሃሳብ “የሰላም ጸር ነው” ብለዋል።

ብሪታንያ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀችው የዩክሬን ድንበሮች በዩክሬን ብቻ እንደሚወሰኑ ገልፃ፥ ማንኛውም የሰላም ስምምነት በዩክሬን ተሳትፎ መገንባት አለበት ብላለች።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ቱስክ በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ አርብ ዕለት ከሚደረገው ስብሰባ በፊት ሰኞ ዕለት ከአውሮፓ አጋሮች ጋር ለመምከር ቃል ገብታ እንደነበር ገልጸዋል።

12 Aug 2025, 15:25