በጋና የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ በግጭት ውስጥ ያለችው ሃገሪቷ ለተፈናቀሉ ሰዎች ለምታደርገው አቀባበል ምስጋና አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሰሜን ምስራቅ ጋና ውስጥ በምትገኘው፣ የባውኩ መንደር ሶስት ወጣቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ በጋና ሰሜናዊ ምስራቅ ክፍል ለረጅም ጊዜ የቆየው ግጭት ዳግመኛ መቀስቀሱ የተነገረ ሲሆን፥ የአከባቢው ባለሥልጣናት የሰዓት እላፊ ገደብ ተግባራዊ በማድረግ እና የጸጥታ አስከባሪዎችን በአካባቢው ላይ በማስፈር ሁኔታውን ለማረጋጋት እየጣሩ እንደሆነ ተነግሯል።
በጋና በስተሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ባውኩ በተባለች ግዛት የተፈጠረውን ጎሳን መሰረት ያደረገውን ግጭት ለማብረድ የሃገሪቱ መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱን ወደ አከባቢው ማዝመቱን ያስታወቀ ሲሆን፥ ከድሮ ጀምሮ በአካባቢው በሚኖሩ ሁለት ጎሳዎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች የሚፈጠሩ ቢሆንም ሰሞኑን በተፈጸመ ጥቃት ግን ተማሪዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁሐን ዜጎች መገደላቸው ተነግሯል።
የእነዚህ ሶስት ወጣቶች መገደል በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የማምፕሩሲ እና የኩሳሲ ጎሳዎች መካከል ለአስርት ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ግጭት ዳግመኛ መቀስቀሱ የተገለጸ ሲሆን፥ ከታሪክ አኳያ የማፕሩሲ ጎሳዎች በባውኩ ግዛት ላይ ባህላዊ ሥልጣን እንዳላቸው ሲከራከሩ፥ በአንፃሩ ኩሳሲዎች እንደ አብዛኛው ሕዝብ በአከባቢው ላይ መብት እንዳላቸው ይሟገታሉ።
በዚህ ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት በአካባቢው የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ በመስጠትና አካባቢው ላይ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ፊደስ የተባለው የቫቲካን የዜና ወኪል እንደዘገበው የጋና የላይኛው ምስራቅ ክልል ሚኒስትር ቤተክርስቲያኒቱ በአከባቢው ላይ ሰላምን ለማስፈን የምትተገብራቸውን ሥራዎች ማድነቃቸውን ገልጿል።
ይሄንን ግጭት ተከትሎ በጋና የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጁሊየን ካቦሬ በግጭት የተመሰቃቀለውን ይህን የጋና ሰሜናዊ ምስራቅ ክፍል የጎበኙ ሲሆን፥ ፊደስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ይህ አካባቢ ከቡርኪና ፋሶ የሚደርስባቸውን ጥቃትን ሸሽተው የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስላማዊ ቡድኖች የሚኖሩበት በመሆኑ በዚህ ሥፍራ ላይ ሌላ ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ገልጿል።
በአከባቢው የምትገኘው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ተጽእኖ ተጠቅማ በአከባቢው ላይ ሰላም እንዲመጣ እና ህዝቡ ወደ አንድነት እንዲመለስ ጥረት እንድታደርግ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ፣ “በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ሁለቱ አካላት ከፖለቲከኞች ይልቅ የሃይማኖት መሪዎችን ድምፅ የመስማት ፍላጎት አላቸው” ብለዋል።
ይህ ግጭት የጀመረው ከቅኝ ግዛት በፊት በነበሩት ጊዜያት እንደሆነ መረጃዎች የሚያመላክቱ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 1957 ዓ.ም. ጋና ነፃነቷን ካገኘች በኋላ አንዱ ጎሳ በሌላኛው ላይ የበላይነቱን ለማረጋገጥ በሚደረግ የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉ ይገለፃል።
ሊቀ ጳጳስ ካቦሬ ለጋና መንግሥት እና ለሰሜናዊ ምሥራቅ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ‘በቡርኪና ፋሶ ያለውን ያልተረጋጋ ሁኔታ ሸሽተው ለተሰደዱት ሰዎች የተደረገውን መስተንግዶ እና ድጋፍ’ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ተጠናክሮ በቀጠለው ግጭት መካከል በችግር ላይ ያሉ ስደተኞችን ለመቀበል እና ለማስጠለል ሀገሪቱ ለምታደርገው የማያወላውል ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።