የመብት ተሟጋች ቡድኖች እስራኤል ወደ ጋዛ የሚደርሰውን እርዳታ የማቋረጧን ተግባር 'የረሃብ ፖሊሲ' በማለት ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምግብ የጫኑ 14 ተሽከርካሪዎች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ቢልክም ተሽከርካሪዎቹ በዋዲ ጋዛ የፍተሻ ጣቢያ ለሶስት ስዓታት ከቆዩ በኋላ እንዲመለሱ መደረጉን የጠቆመው ተቋሙ፥ በርካታ ሰዎች ተሽከርካሪዎቹን አስቁመው ከ200 ቶን በላይ ምግብ መዝረፋቸውን ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡትን የጋዛን የመጀመሪያውን ምዕራፍ ማራዘም ሐማስ አለመቀበሉ ይህንን የእርዳታ እገዳ እርምጃ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስቴ ቤኒያሚን ኔታንያሁ ገልጸዋል። ሐማስ ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋስትና ከአሸማጋዮቹ ካላገኘ አንደኛው ምዕራፍ እንዲራዘም አልስማማም ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ሙሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቋረጥ ያደረገችው በአሜሪካ የቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም አንደኛ ምዕራፍ የማራዘም ሃሳብ ሐማስ አለመቀበሉን ተከትሎ ነው።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅቶች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የሰብአዊ ድጋፍ በብዛት እንዲገባ ቢጠይቁም ተፋላሚዎቹ እስካሁን ስምምነት ላይ አልደረሱም።
በረመዳን ጾም መጀመሪያ ይደረሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የተኩስ አቁም ድርድርም በካይሮ ያለ እስራኤል ተሳትፎ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃማስን የእስራኤል-ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማራዘም አሜሪካ ያቀረበችውን ሀሳብ ውድቅ አድርጓል በማለት እና የምግብ አቅርቦቶችን ዘርፏል በሚል እርዳታ ወደ ጋዛ እዳይገባ መከልከላቸውን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ላይ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እና የማህበረሰብ ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች ክምችት መሟጠጡን ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐማስ የእርዳታ አቅርቦቱን በመስረቅ “የሽብር ተግባሩን” ለመደገፍ እየተጠቀመበት ነው ሲሉ ወንጅለው ማንኛውም እርዳታ እንዳይገባ እግድ ጥለዋል።
ሐማስ በበኩሉ እስራኤል የተኩስ አቁሙን ለማደናቀፍ እየወሰደችው ያለው እርምጃ እንደሆነ እና ድርጊቱ “የጦር ወንጀል እንደሆነ” እና “በተኩስ አቁሙ ላይ የተካሄደ ቀጥተኛ ጥቃት ነው” ሲል ከሷል።
እስራኤል 2 ሚሊዮን ለሚሆነው የጋዛ ህዝብ ይደርስ የነበረውን የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና ሌሎች አቅርቦቶችን ማቋረጧ በአከባቢው የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉን እና በአሁኑ ወቅት ሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ቡድኖች እየመነመነ ካለው ክምችቶቻቸው በመውሰድ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ለማሰራጨት እየሞከሩ እንደሆነ ተገልጿል።
ወደ ሰርጡ የሚገባው ዕርዳታ በመቆሙ ምክንያት የረድኤት ሰራተኞቹ እስራኤል እና ሃማስ ጥር ወር ላይ ባደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነት ምዕራፍ አንድ ላይ በነበሩት ስድስት ሳምንታት ረሃብን ለመታደግ ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት እንዳጨናገፈባቸው አሳውቀዋል።
የተኩስ አቁሙ ለ15 ወራት የዘለቀውን የጋዛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ ሲሆን፥ በዚህም 33 እስራኤላዊ ታጋቾች እንዲሁም በእስራኤል እስር ቤት ያሉ 1 ሺህ 900 ፍልስጤማውያን ተለቀዋል።
ለ16 ወራት በላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የጋዛ ህዝብ ሙሉ በሙሉ በጭነት መኪና ተጭነው በሚገቡ ምግቦች እና ሌሎች እርዳታዎች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ አብዛኛው ህዝብ ከመኖሪያ ቤቱ በመፈናቀሉ ምክንያት ጊዜያዊ መጠለያ እደሚያስፈልገው የረድኤት ሰራተኞች ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ነዳጅ የሚያስፈልገው የጭነት መኪናዎች እርዳታ እንዲያደርሱ ለማስቻል ብቻ ሳይሆን ሆስፒታሎች፣ የውሃ ፓምፖች፣ ዳቦ ቤቶች እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ጭምር እንደሆነ ተገልጿል።
እስራኤል የእገዳው እና ከበባው ዋና ዓላማ ሃማስ የዩናይትድ ስቴትስን የተኩስ አቁም የማራዘሚያ ሃሳብ እንዲቀበል ግፊት ማድረግ እንደሆነ እየገለጸች ሲሆን፥ እስራኤል ከሃማስ ጋር የገባችውን የዕርዳታ ፍሰቱ እንዲቀጥል የሚያስችለውን የሁለተኛ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እንደዘገየች ተነግሯል።
‘የረሃብ ፖሊሲ’
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት በሃማስ ላይ የሚያደርጉትን ጫና አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ገልጸው፥ ሃማስ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተስማማ ወደ ጋዛ የሚገባውን የኤሌክትሪክ ሃይል እንደማያቋርጡ ቃል ገብተዋል።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች እስራኤል በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ዙሪያ የያዘችውን አቋም “የረሃብ ፖሊሲ” ብለው የገለጹ ሲሆን፥ የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጊዜ ካለቀ ከአራት ቀናት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና የምግብ ኤጀንሲ የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደገለጸው በምዕራፍ አንዱ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ሁሉንም የእርዳታ ምግብ ለተራቡ ሰዎች በማከፋፈል ላይ ትኩረት አድርጎ ስለነበረ በአሁኑ ወቅት በጋዛ በቂ የሆነ የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት እንደሌለው በመግለጽ፥ አሁን ያሉት ክምችቶች ለዳቦ መጋገሪያዎች እና ምግብ አብሳይ ቡድኖች ከሁለት ሳምንታት ላነሰ ጊዜ ብቻ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ በቂ ናቸው ብሏል።
የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት በበኩሉ እንደገለጸው፣ በጋዛ ውስጥ ምንም ዓይነት መጠባበቂያ የድንኳን ክምችት እንደሌለው በመግለጽ፥ በምዕራፍ አንዱ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ላይ የገቡት የመጠለያ ቁሳቁሶች በቂ እንዳልነበሩ አመልክቷል።
የድርጅቱ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እንደተናገሩት ክምችቱ በቂ ቢሆን ኖሮ “በመጠለያ ቁሶች እና ብርድ ልብሶች እንዲሁም ተገቢ የህክምና መሳሪያዎች እጥረት የተነሳ የሚሞቱ ጨቅላ ህጻናት አይኖሩም ነበር” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።