የኩባ መንግሥት የኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ እስረኞችን የሚፈታ መሆኑ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የኩባ መንግሥታ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 553 ሰዎችን ከእስር እንደሚፈታ ሲያስታውቅ፥ ውሳኔው የተነገረው የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፃፉት ደብዳቤ ሲሆን፥ እስረኞቹ የሚፈቱት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በያዝነው 2025 ዓ. ም. በሚከበረው መደበኛ የኢዮቤልዩ በዓል መንፈስ እንደሆነ ገልጿል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፥ እስረኞቹ የሚፈቱት የኩባ መንግሥት ከቫቲካን ጋር በመሠረተው ቅርብ እና ፈጣን ግንኙነት መሆኑን ገልጾ፥ በሀገሪቱ እና በቫቲካን መካከል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያደረጋቸው ግንኙነቶችን ዘረዝሯል።
በተለይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ ወር 2022 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በኩባው ፕሬዝዳንት አቶ ዲያዝ ካኔል መካከል በተካሄደው ስብሰባ የእስረኞችን ችግር እና እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
የአሜርካ መንግሥት ኩባን ከሽብር ደጋፊነት መዝገብ አውጥታለች
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፥ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባመቻቸችው ስምምነት መሠረት ኩባን ከሽብርተኛ ደጋፊ መንግሥትነት ስያሜ ለማንሳት ያላቸውን ፍላጎት በዋይት ሃውስ ለኮንግረሱ ማሳወቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል። እስረኞቹ በመጪዎቹ ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈቱ ሲጠበቅ፥ አንዳንዶች የባይደን የስልጣን ጊዜ በጥር 12 ከማብቃቱ በፊት ነፃ መሆናቸው ታውቋል።
የኩባ መንግሥት መግለጫ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው፥ ሀገሪቱ "ከቫቲካን እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተከበረ፣ ግልጽ እና ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንዳላት ገልጾ፥ ይህም በቅርቡ የተወሰደውን ውሳኔ የሚያመቻች ነው” ሲል አስታውቋል።
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢዮቤልዩ ዓመት እስረኞች እንዲፈቱ ተማጽነዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢዮቤልዩ ዓመትን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ “መንግሥታት ተስፋን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ የታቀዱ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ፤ ይህም ግለሰቦች በራሳቸው እና በኅብረተሰቡ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት የታሰበ የምሕረት ወይም የይቅርታ ዓይነት እንዲሆን በማለት ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የኩባ መንግሥት እስረኞችን መፈታቱ ከዚህ ቀደም ከሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጋቸው ግንኙነቶች ምልክት እንደ ሆነ አስታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1998 ዓ. ም. የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ኩባን በጎበኙበት ወቅት፣ ፊደል ካስትሮ ወደ 200 የሚጠጉ እስረኞችን መፍታታቸው ይታወሳል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2012 ዓ. ም. የቀድሞው ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ኩባን በጎበኙበት ዋዜማ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ነፃነታቸውን የተጎናፀፉ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብሎ ወደ 3,500 ገደማ የሚሆኑ እስረኞች በነፃ መለቀቃቸው ይታወሳል።
በኩባ እና ዋሽንግተን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ ወር 2014 ዓ. ም. ወደ ነበረበት መመለሱ ይታወሳል። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ባራክ ኦባማ እና የኩባው አቻቸው ራውል ካስትሮ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስምምነቱ ላይ እንዲደርሱ ላደረጉት አስተዋፅኦ ማመስገናቸውም ይታወሳል።