የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

በኳታር እየተካሄደ ያለው የተኩስ አቁም ንግግር ለጋዛ ብሩህ ተስፋን ሊያመጣ እንደሚችል ተነገረ

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተካሄደ ያለው የተኩስ አቁም ንግግር ወሳኝ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት ኳታር የስምምነቱን የመጨረሻ ረቂቅ አቅርባለች። በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ወዲህ ከ46,000 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበትን ጦርነት ማስቆም ከምን ጊዜውም በበለጠ አስቸኳይ ሆኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረሱ ሲነገር፥ ሰኞ ጥር 5/2017 ዓ. ም. ከተካሄደው የሰላም ድርድር በኋላ ኳታር ለእስራኤል እና ለሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጨረሻ ረቂቅ እቅርባለች። በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ የተካሄደው ንግግር የእስራኤል እና የሃማስ ተወካዮች ጨምሮ የተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዑካንን ያካተተ እንደ ነበር ታውቋል።

ሮይተርስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው፥ በውይይቶቹ ላይ የተሳተፈ አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን ዕድገቶቹ ተስፋ ሰጭ ናቸውን ማለታቸው ግልጾ፥ ብሩህ ተስፋ የሚታይባቸው፣ ክፍተቶችም እየጠበቡ መሆናቸውን እና እስከ መጨረሻው ሁሉም ነገር ጥሩ ከሆነ ስምምነት ላይ ለመድረስ ትልቅ ግፊት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን ገልጿል።

በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት
የእነዚህ ንግግሮች አጣዳፊነት በቃላት ሊገለጽ እንደማይችል የተገለጸ ሲሆን፥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ወዲህ ጋዛ ውስጥ ከ46,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። በጋዛ ሰርጥ መሠረተ ልማት ፈርሷል፤ ሙሉ በሙሉ ውድመት ያልደረሰባቸው ጥቂት ሆስፒታሎች የእስራኤልን ጥቃት ለመቋቋም እየታገሉ ይገኛሉ፤ እንደ ምግብ፣ ውሃ እና መብራት ያሉ የአስፈላጊ አቅርቦቶች ተደራሽነት በጣም ውስን ነው። ሰብዓዊ ቀውሱ በየሰዓቱ እየተባባሰ ይገኛል፤ በመሆኑም የተኩስ አቁም ንግግሮች የሰውን ሕይወትን ከሞት ለማትረፍ የግድ አስፈላጊ መሆናቸው ታውቋል።

ወደ ሰላም የሚደረግ እርምጃ
ሌላው ለታቀደው ስምምነት መሠረታዊ እርምጃ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ኔታንያሁ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልክ ተወያይተዋል። ስምምነቱ በሐማስ ከ15 ወራት በላይ ተይዘው ከቆዩት 33 ታጋቾች ጋር የቆሰሉትን የእስራኤል ወታደሮች ለማስለቀቅ እና እስራኤል በበኩሏ ከ3,000 በላይ የፍልስጤም እስረኞችን ለመልቀቅ መስማማቷን ይገልጻል። ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚሆኑት የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ታውቋል። አብዛኞቹ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከባድ ቅጣት የሚደርስባቸው እንደ ኳታር፣ ግብፅ ወይም ቱርክ ወደመሳሰሉት አገሮች ሊሰደዱ እንደሚችሉ ተነግሯል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ጥር 17/2017 ዓ. ም. አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታቀዶ የነበረው ተጨማሪ የቅርብ ጊዜ ክንውን ይገኝበታል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለውይይት ቅድመ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ለእንደዚህ ዓይነት ስምምነቶች ግልጽነት ሲያሳዩ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሯል።

በአካባቢው ያለው የፖለቲካ ምህዳር ለለውጥ ክፍት እየሆነ በመጣበት በዚህ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም የሚያቀርቡትን የማያቋርጥ ጥሪ በጽናት የቀጠሉ ሲሆን፥ ባለፈው እሑድ ባቀረቡት ጥሪ፥ ጦርነት ምን ጊዜም ሽንፈት እንደሆነ በድጋሚ በማሳሰብ ምዕመናኑ ለዓለም ሰላም በተለይም ለመካከለኛው ምሥራቅ ጸሎት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።


 

14 January 2025, 17:03