ብጹዕ ካርዲናል ሙላ፥ ደቡብ ሱዳናውያን ከአሰቃቂ ግድያ በኋላ የበቀል እርምጃ እንዳይወስዱ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅርቡ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ፥ የሱዳን ጳጳሳት ጉባኤ (ኤስኤስኤስ-ሲቢሲ) ፕሬዚደንት ብፁዕ ካርዲናል ሙላ፥ ዜጎቹ በደረሰባቸው ከባድ ሕመም ውስጥ ቢሆኑም የበቀል እርምጃ ሊወስዱ እንደማይገባ ተማጽነዋል።
ብጹዕ ካርዲናሉ ሙላ በስደተኞቹ ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ አውግዘው፥ በንጹሃን የደቡብ ሱዳን ዜጎች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ፥ “ከጥላቻ እና ከጭቆና የመነጨ አስጸያፊ ተግባር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፍቅርን፣ ይቅርታን እና መግባባትን መቀበል
በደቡብ ሱዳን የጁባ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሙላ በደቡብ ሱዳናውያን ላይ የሚፈጸመውን የጥቃት እርምጃ የሚመራ ኃይል ግለሰቦችን በብሔራቸው፣ በእምነታቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ የጨቋኝ ሥርዓቶች ውጤት መሆናቸውን በማስረዳት፥ “ጥሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምረን በፍቅር፣ በይቅርታ እና በመግባባት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ነው” ብለዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ሙላ በመግለጫው። “ከእነዚህ እኩይ ድርጊቶች አንፃር የምንወዳቸው የደቡብ ሱዳን ወገኖቻችን መጽናናትን እና ርኅራሄን እንዲላበሱ፣ ከእነዚህ ክስተቶች የሚመጡ ስቃዮችን እና ቁጣዎችን መረዳት ከባድ ቢሆንም በደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ እንደሚገባ ተማጽነዋል።
አያይዘውም፥ “ከገዛ አገራቸው ከሚሸሹት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በኛም ላይ ጥቃት የሚፈጽም ተመሳሳይ ግፈኛ መንግሥትን የሚቃወሙ እና ምሕረት የሌለው የጨካኝ ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው” ብለዋል።
መበቀል ይጎዳል!
በቀል እንደሚፈጸም ሥጋት እንዳላቸው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ሙላ፥ በቀል ግጭትን እና ጥላቻን እንደሚያባብስ ተናግረው፥ ሕዝቦችን የበለጠ ወደ ብጥብጥ እና ወደ ስቃይ በማምራት የጥላቻn አዙሪት እንደሚያሰፋ አስረድተዋል። ከበቀል ይልቅ ችግርን እንደ አንድ የጋራ ሰብዓዊ ተሞክሮ በመመልከት በመካከላችን መጠለያ ለሌላቸው የርርርዳታ እጃችንን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ መደጋገፍ ያስፈልጋል
ብፁዕ ካርዲናል ሙላ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ላለው የአንድነት መንፈስ አድናቆታቸውን ገልጸው፥ በሐዘን የተጎዱ ቤተሰቦችን እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠዋል። በቀጣይም ውይይትን በማስፋፋት ርኅራኄን እንዲያጎለብቱ እና እርስ በርስ የሚገናኙበትን ድልድይ እንዲገነቡ ጠይቀዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ሙላ አክለውም፥ በእነዚህ ተግባሮቻቸን አማካይነት ሕይወታቸውን ያጡትን በማስታወስ ሰላም፣ ፍትህ እና እርቅ የሰፈነበት ዘመን እንዲመጣ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል። የተጎጂ ቤተሰቦችን በጸሎት በማሰብ በዚህ ሊቋቋሙት በማይችሉት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች ጎን መቆማቸውን ገልጸው፥ የደቡብ ሱዳን ማኅበረሰቦች በሚያሳዩት የአንድነት እና የፅናት መንፈስ እንደሚኮሩ፣ መነሻቸው ምን ይሁን ምን እያንዳንዱ ግለሰብ ደህንነቱ የሚጠበቅበትን እና የሚከበርበትን አካባቢ በማጎልበት ወደ ፈውስ እና መልሶ ግንባታ መሥራት እንደሚገባ አደራ ብለዋል።