ዩኒሴፍ ናይጄሪያ ለህጻናት ጥበቃ ወሳኝ እርምጃ እንድትወስድ ጥሪ አቀረበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፉት አስር አመታት በሃገሪቷ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ በተፈፀሙ የተለያዩ ጥቃቶች 180 ህጻናት ሲገደሉ ከ1680 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታግተዋል።
ዩኒሴፍ ናይጄሪያ በቅርቡ ባወጣው አዲስ ሪፖርት ከ70 በላይ የትምህርት ቤት ጥቃቶች መከሰታቸውን በመግለጽ፥ 60 የሚሆኑ የትምህርት ቤት ሰራተኞች መታገታቸውን እና 14ቱ ደግሞ መገደላቸውን አረጋግጧል።
ሪፖርቱ የወጣው በቦኮ ሃራም እስላማዊ አሸባሪ ቡድን በቺቦክ ቦርኖ ግዛት አብዛኞቹ ክርስቲያን የሆኑበት 276 ሴት ተማሪዎች የታፈኑበትን አሥረኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ እና ባለፈው ወር በካዱና ግዛት በሚገኘው ትምህርት ቤት ልጆች ላይ የተፈፀመውን ሌላ አፈና ተከትሎ መሆኑም ተገልጿል።
ጥቃቶች እና ጠለፋዎች አንዳንድ ጊዜ ከርዕዮተ ዓለም ወይም ከማህበራዊ ግጭቶች ጋር የተያያዙ ቢሆኑም፥ አብዛኛዎቹ ግን የሚፈፀሙት ኢኮኖሚያዊ ዓላማ ባላቸው እና ታጋቾችን በርከት ባለ ገንዘብ ለመቀየር ተስፋ ባደረጉ ወንጀለኛ ቡድኖች እንደሆነም ይነገራል።
በልጆች ደህንነት ላይ በሚደርሱ አደጋዎች ምክንያት የትምህርት አሰጣጡ አደጋ ላይ ነው
‘በናይጄሪያ ውስጥ ደህንነታቸው የተጠበቁ ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛው መመዘኛዎች’ ተብሎ በወጣው የስድስት ወራት የክትትል ሪፖርት በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኙ አስር ግዛቶች ውስጥ የመንግስት ዝቅተኛ ደረጃዎች አፈፃፀም “ለመገምገም የተደረገውን የጥናት ውጤት” ጠቅለል አድርጎ አሳይቷል።
እንደቀረበው ሪፖርት ከሆነ “የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መስፋፋት እና የጾታ እኩልነትን ጨምሮ፥ ናይጄሪያ ትምህርትን በማሳደግ ረገድ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች በልጆች ደኅንነት ላይ በሚታዩ ተጨባጭ አደጋዎች ስጋት ላይ መውደቁን ያሳያል ተብሏል።
ሪፖርቱ በሰሜናዊ ምዕራብ የሃገሪቱ ክልል ለረጅም ጊዜያት የተከሰቱት ግጭቶች በትምህርት ቤቶች ላይ የሚፈጸሙ ቀጣይ ጥቃቶች እንዲሁም የህፃናት እና መምህራን ግድያ እና አፈና እንዲባባስ ማድረጉን አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፥ እንዲሁም እየተከሰተ ባለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር የተያያዙ ውጥረቶችም መባባሱን ገልጿል።
ዩኒሴፍ ናይጄሪያ እንደጠቆመው በእነዚህ ምክንያቶች በ2012 ዓ.ም. ብቻ ወደ 11,500 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በሚደረሱት ጥቃቶች ምክንያት የተዘጉ ሲሆን፥ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናት ጥቃቶቹን ፈርተው ወደ ትምህርት ገበታ እንዳልተመለሱ ገልጿል።
መንግስት በአስቸኳይ ለደህንነት ቅድሚያ መስጠት አለበት
ናይጄሪያ ለትምህርት ቤቶች ደህንነት መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ተቋማዊ ለማድረግ ያሳየችው መነሳሳት የሚያስመሰግን እርምጃ እንደሆነ የዩኒሴፍ ዘገባ ያመላከተ ሲሆን፥ ይሄንን ቁርጠኝነት ጥናቱ በተካሄደባቸው ሁሉም ግዛቶች ውስጥ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው መቆጨቱን ገልጿል።
በናይጄሪያ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ክሪስቲያን ሙንዱዋቴ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት ተጨማሪ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት በመግለጽ፥ “በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የደህንነት ጥበቃ ጥረቶችን ለማሳደግ በአስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ካሉ በኋላ፥ “ድርጅታቸው የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር፣ የክልል እና የአካባቢ የትምህርት ባለስልጣናት፣ ማህበረሰቦች እና ትምህርት ቤቶች ለእያንዳንዱ ልጅ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ ለሚደርጉት ጥረት ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል” በማለት ተወካይዋ የድርጅታቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ገልጸዋል።