የአርመን ፖሊስ በመዲናዋ ዬሬቫን ከተማ መሀል በተጠንቀቅ ቆመው የአርመን ፖሊስ በመዲናዋ ዬሬቫን ከተማ መሀል በተጠንቀቅ ቆመው   (AFP or licensors)

በናጎርኖካራባክ በተከሰተው ግጭት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞቱ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረገ

ባለስልጣናት እንዳሉት የአዘርባጃን ጦር በናጎርኖ ካራባክ አካባቢ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሞቱበትን ጥቃት ከከፈተ ከ24 ሰዓት በኋላ የአርሜኒያ ጎሳ አባላት በሩሲያ አማካይነት በቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በደቡብ ካውካሰስ ግዛት ማክሰኞ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 32 ሰዎች መሞታቸው እና ወደ 200 የሚጠጉት ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአዘርባጃን ክልል የሆነችው በናጎርኖ ካራባክ ዋና ከተማ ስቴፓናከርት በአርመን ጎሳዎች እና በአዘርባጃን ሀይሎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት ፍንዳታዎች ይሰሙ ነበር።
አዘርባጃን ወደ ግዛቷ የሚገባውን ቁልፍ መንገድ በመዝጋቷ ወደ 120,000 የሚጠጉ አርመኖች ያለ በቂ ምግብ እና መድሃኒት ከውጭው ዓለም በተቆራረጡበት አካባቢ ትናንት መስከረም 9 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈጽሟል።
በሁለቱም አዘርባጃን መንግስት እና አርሜኒያ ጎሳዎች መካከል የናጎርኖ-ካራባክ ክልልን የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል።
ማክሰኞ ዕለት አዘርባጃን ‘ፀረ-ሽብርተኛ’ በማለት የጠራችውን ወታደራዊ ዘመቻ በአወዛጋቢው ክልል ጀምራለች።
በናጎርኖ ካራባክ ደ-ፋክቶ ዋና ከተማ ስቴፓናከርት ድንገተኛ የሆኑ የቦንብ ጥቃት ፍንዳታዎች እና የመድፍ ድምፆች ይሰሙ ነበር ተብሏል።
በተጨማሪም ድሮኖች የአርመን አየር መከላከያ ቦታዎችን ለመምታት ጥቅም ላይ ውለዋል። አንድ በአከባቢው የነበረ ምስክር እንደገለጸው የ ‘ግራድ ሚሳኤሎች’ ድምጽ ይሰሙ እንደነበር እና ከተራራማው አከባቢ ጭስ ይታይ እንደነበረም ገልጿል። በዚህም የአዘርባጃን ዘመቻ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው እና በርካቶችም መቁሰላቸው ተነግሯል።

ምንም አይነት ወታደራዊ መሳሪያዎች የሉም

የስቴፓናከርት ነዋሪ የሆነው ዴቪድ በጥቃቱ የወደሙ ቤቶች አጠገብ ቆሞ እንደተናገረው “እዚህ ምንም አይነት ወታደራዊ መሳሪያዎች የሉም ፥ እዚህ የመኖሪያ ቤቶች ብቻ ናቸው ያሉት ፥ በህንፃው ውስጥ ጡረተኞች እና አካል ጉዳተኞች ናቸው የሚኖሩበት” ብሏል።
ሆኖም የአዘርባጃን መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ኦፕሬሽኑ የጀመረው በናጎርኖ ካራባክ ክልል በተፈፀመ የፈንጂ ጥቃት አራት ወታደሮች እና ሁለት ሲቪሎች ከሞቱ ከሰዓታት በኋላ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ ገልጿል።
የአርሜኒያ ሃይል ሩሲያ በጉዳዩ ጣልቃ እንድትገባ ቢጠይቅም እዚያ የሰፈሩት 2,000 ያህል የሚሆኑ የሩስያ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጥቃት እስካልተፈጸመባቸው ድረስ ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ እንደማይችሉ ነው የተነገረው።
ክሬምሊን 'አዘርባጃን ‘በግዛቷ ላይ’ ነው ዘመቻውን ያካሄደችው' በማለት የባኩን (የአዘርባጃን ዋና ከተማ) ድርጊት በዘዴ ስታፀድቅ ታይቷል።
ሩሲያ በናጎርኖ-ካራባክህ ጉዳይ ያሳየችው አቋም አዲስ አይደለም። ተቺዎች እንደሚሉት ሞስኮ በዩክሬን እያደረገችው ባለው ጦርነት ምክንያት ትኩረቷ ስለተከፋፈለ ፥ አዘርባጃን ባለፈው የፀደይ ወቅት በላቺን ኮሪደር ላይ አዲሱን የደህንነት ፍተሻ ጣቢያ ባቋቋመችበት ወቅት ምንም ዓይነት ተቃውሞ አላሰማችም ነበር። በዚህም ጣቢያ ምክንያት በአርሜኒያ እና በአካባቢው መካከል የሰዎች እና የሸቀጦች ፍሰት መቋረጡ ተነግሯል።

አሁንም ስጋቶች አሉ

የተኩስ አቁም ቢታወጅም ፥ በአካባቢው ያሉ አርመኖች አርትሳክ ብለው በሚጠሩት በታገደው ክልል ያለው ውጥረት ፥ የሶቭየት ኅብረት ውድቀትን ተከትሎ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እና ቀደም ሲል በ1990ዎቹ የተካሄደውን የትጥቅ ግጭት እንደገና ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይህም ፍርሃት በአርሜኒያ ዋና ከተማ ዬሬቫን ጎዳናዎች ላይም ተስፋፍቷል።
በዬሬቫን በሚገኘው የፓርላማ ሕንፃ ደጅ ላይ ከፖሊሶች ጋር የተፋጠጡት ተቃዋሚዎች በናጎርኖ-ካራባክ ውስጥ ለአርሜኒያውያን ተጨማሪ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን እንደተናገሩት ‘የዬሬቫን መንግስት በናጎርኖ ካራባክ አካባቢ በሚገኙ ተገንጣዮች እና በአዘርባጃን መንግስት መካከል የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሰነድን በማዘጋጀት አልተሳተፈም’ ካሉ በኋላ ፥ ‘ሆኖም ስምምነቱ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ’ ብለዋል።
መጪው ጊዜ በእርግጠኝነት ምን እንደሚከሰት ባይታወቅም ፥ ሩሲያ ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያከብሩ ማሳሰቧ ተነግሯል።
 

21 September 2023, 16:21