ፈልግ

በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የአትክልት ሥፍራ በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የአትክልት ሥፍራ   (Governatorato_SCV)

በቫቲካን የሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአትክልት ሥፍራ መሉ በሙሉ ኦርጋኒክ መሆኑ ተገለጸ

በመካከለኛው ዘመን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኒኮላስ ኦርሲኒ ሦስተኛ ትዕዛዝ የተዘጋጀው የቫቲካን የአትክልት ሥፍራ “ውዳሴ ላንተ” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ በተገለጸው ፍጥረትን በመንከባከብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ኦርጋኒክ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን የአትክልት ሥፍራዎች ውስጥ ከ“ማተር ኤክለሲያ” ገዳም አጠገብ የሚገኘው የአትክልት ሥፍራ ሙሉ በሙሉ ኦርጋኒክ እየሆነ የመጣ ሲሆን፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ የአካባቢ ጥበቃን በማስመልከት “ውዳሴ ላንተ” በሚል ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ እንደተጠቀሰው የእርሻ ሥራ ዓላማ ከፍተኛ ምርትን ማግኘት ሳይሆን የእያንዳንዱን ተክል እና የአፈር የተፈጥሮ ዕድገት ዑደቶችን ማክበር እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ኅዳር ከጣሊያን የግብርና እና የደን ባለሙያዎችን ጋር በተገናኙበት ወቅት ለፍጥረት እንክብካቤ አፅንዖት መስጠታቸው ሲታወስ፥ ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ለእናት ምድራቸው እና ለወደፊት ትውልዶች የሚደረግ ተጨባጭ የበጎ አድራጎት አድርገው እንዲመለከቱት በማሳሰብ፥ “ምድር ንብረት ሳትሆን ስጦታ በመሆኗ በአክብሮት እና በጥበብ የሚያርሱት በሙሉ በእግዚአብሔር የፈጠራ ሥራ ውስጥ ይሳተፋሉ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

መሬትን የሚያከብር የእርሻ ዘዴ

ቀደም ሲል በካስቴል ጋንዶልፎ ከሚገኙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሕንጻዎች የሚወጣ ፍግ ለአትክልት እንደ ማዳበሪያነት ይውል እንደ ነበር ሲታወቅ ነገር ግን ዛሬ የእፅዋትን ፍላጎቶች የሚያሟሉ የማዳበሪያ ዓይነቶች ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል።

የአፈርን ልምላሜ መጠበቅ የሚቻለው እንደ አረንጓዴ የባቄላ ተክል በተፈጥሮ ናይትሮጅን የሚያድጉ ጥራጥሬዎችን ማፈራረቅ ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲሆን፥ ዘንድሮ የባሕር ውስጥ ተክሎችን እንደማዳበሪያነ በቲማቲም እርሻ እየተሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል።

ከውጭ የሚመጡ ችግኞች በተፈጥሮ ዘዴዎች የሚታከሙ ሲሆን፥ መላውን ሰብል ሊያበላሹ የሚችሉ የእፅዋት በሽታ መዛመትን ለመገደብ በቤት ውስጥ ከሚያድጉ ችግኞች ይልቅ ተገዝተው የሚመጡ ችግኞች እንደሚመረጡ ታውቋል።

መነኮሳቱ ከአትክልተኛው እና ረዳቶቹ ጋር በኅብረት ይሠራሉ

አትክልተኛውን የሚያግዙ ገዳማውያትም ከጊዜ ወደ ጊዜ የትኞቹ ሰብሎች እንደሚያስፈልጉ የሚያሳዩት ሲሆን፥ ወቅቱ እና መሬቱ በዚያ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ምን ሊቀርብለት እንደሚችል የሚለውን ግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ ታውቋል።

ወቅቱን ጠብቀው የሚደርሱ ምርቶች

የእርሻ ጊዜ ከተለያዩ ወቅቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው ሲሆን፥ ነጭ ሽንኩርት፣ ባሲል፣ የቺሊ ቃሪያ፥ በጥንካሬው የሚታወቅ የፔሩ ዝርያን ጨምሮ የሎረል ፍራፍሬዎች እና ዱባዎች እስከ ኅዳር ወር ድረስ እንደሚደርሱ ተመልክቷል።

በዚህ ዓመት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ የኪዊ ተክሎች በገዳማውያቱ ጥያቄ የተተከሉ ሲሆን በነሐሴ ወር መጨረሻ እና በመስከረም ወር መጀመሪያ መካከል የሳቮይ ጎመን፣ ብሮኮሊ፣ ስፒናች እና ሰላጣን ጨምሮ የክረምት ተከላ እንደሚጀምር ታውቋል።

ግንቦት ወር የአትክልት ሥፍራው ውጤታማ ጊዜ ነው

የበጋ ወቅት በሙቀቱ ምክንያት ለአትክልት ሥፍራ አስቸጋሪው ሲሆን፥ ቲማቲም፣ ኤግፕላንት፣ ቃሪያ፣ አረንጓዴ ባቄላ፣ ዙኪኒ እና ኪያር ከፑሊያ ግዛት የሚመጣ ዝርያን ጨምሮ በዕድገት ዑደታቸው መጨረሻ ላይ የሚደርሱ እንደሆነ ታውቋል።

ባለፉት ዓመታት ከዚህ ትንሽ የአትክልት ሥፍራ የሚገኘው ምርት እንደ “ካዛ ዶኖ ዲ ማርያ” ላሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት ጭምር ምርቶችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህ አገልግሎት አሁን በአዲስ ጉልበት እና ቁርጠኝነት እየተነቃቃ እንደሚገኝ ታውቋል።

የ800 ዓመት ታሪክ ያለው የአትክልት ሥፍራ

የአትክልት ሥፍራው ታሪክ ከመካከለኛው ዘመን የሚጀምር ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኒኮላስ ኦርሲኒ ሦስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1277 እና 1280 ባሉት ዓመታት ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መኖሪያ ቤት ከላቴራን ወደ ቫቲካን ሲያዛውሩ በአዲሱ ግድግዳዎች የታጠረ የፍራፍሬ እርሻ እንዲዘጋጅ ማዘዛቸው ታውቋል። ይህም በጳጳሳዊ መኖሪያ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፍላጎቶችን ለማሟላት የረዳ ውጤታማ ሥፍራ እንደ ነበር ይታወሳል።

ለስምንት መቶ ዓመታት ለነዋሪው ቀለብ ሲሰጥ የቆየው ሥፍራው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1992 እስከ 1994 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይለወጥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ዳግማዊ ስም ከተመሠረተው ገዳም በተጨማሪ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጁ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥፍራዎችን እንደሚካትት ታውቋል።

የአትክልት ሥፍራው በሚገኝበት አካባቢ የሚኖሩ ገዳማውያት “ማልማት በእጅ የሚቀርብ ጸሎት ነው” በሚለው መርህ መሠረት ግብርናን ራሳቸው ይሠሩ እንደ ነበር በወቅቱ የገዳሙ አለቃ የነበሩት የቅዱስ ቤነዲክቶስ ማኅበር አባል እህት ማርያ ሶፊያ ሲኬቲ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 26/2009 ዓ. ም. “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ለተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ በዚህ የአትክልት ሥፍራ በእግር መጓዝን ይወዱ እንደ ነበር ታውቋል።

 

19 Aug 2026, 15:51