ፈልግ

በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያን እና በ ‘ኮንፊሺያን' መካከል የተካሄደ የጋራ ስብሰባ በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያን እና በ ‘ኮንፊሺያን' መካከል የተካሄደ የጋራ ስብሰባ 

የበለጠ ተስማሚ ዓለምን ለመገንባት በጋራ መሥራት ይገባል ተባለ

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ ኩቫካድ በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል በሚገኝ የሶጋንግ ዩኒቨርሲቲ በክርስቲያን እና በ ‘ኮንፊሺያን’ መካከል የሚካሄደውን የመጀመሪያ መደበኛ ስብስውባ በንግግር ከፍተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ በንግግራቸው ሁለቱም የእምነት ተቋማት የሰውን ልጅ ጥልቅ ምኞቶች እንደሚገልጹ ተናግረው፥ ይበልጥ ፍትሃዊ፣ ተስማሚ እና ርኅሩኅ ዓለምን መፍጠር የሚችሉት ሰላማዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ደጋፊ ማኅበረሰቦችን በመገንባት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ አስተያየታቸውን የሰጡት ሐምሌ 28/2018 ዓ. ም. በሴኡል በሚገኘው ሶጋንግ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የክርስቲያን እና የ ‘ኮንፊሺያን’ ስብሰባ weቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው እንደሆነ ታውቋል። እስከ ሐምሌ 29 ድረስ የሚቆየው ስብሰባው በሁለቱ ሃይማኖታዊ ወጎች መካከል የመጀመሪያ የሆነውን መደበኛ ውይይት እንደሚያካሂድ ታውቋል።

የክርስትና እና የኮንፊሺያን ተግባቢ ማኅበረሰብ ፍለጋ

ክርስትና እና ‘ኮንፊሺያኒዝም’ (በማኅበራዊ መግባባት፣ በሥነ-ምግባር እና በሕጎች ማክበር ላይ ያተኮረ የአስተሳሰብ ሥርዓት) ተስማሚ ማኅበረሰብን ለመገንባት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ላይ ውይይት ለማድረግ ከሁለቱ ሃይማኖቶች እና ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሰዎች የየራሳቸውን ወጎች አስተዋፅዖ ማድረጋቸው ታውቋል።

የበጎነት እና የአገልግሎት ሕይወትን የሚያበረታቱ ባሕሎች

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ በንግግራቸው፥ ሁለቱ የዓለም ታላላቅ የስልጣኔ ወጎች የኅብረተሰቦችን የሞራል፣ የባህልና የማኅበራዊ ዕድገት በጥልቅ እንደቀረጹ እና በጎነትን እና የጋራ ጥቅምን ማገልገል እንደቀጠሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“በሁለቱ ወጎች መካከል የተደረገው ውይይት እስካሁን ድረስ ውስን ሆኖ ቆይቷል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ፥ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት በጋራ መከባበር ለወንድማማችነት እና ለሰው ልጅ ሙሉ ዕድገት በተሰጠ የጋራ ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

በማከልም የ ‘ኮንፊሺያን’ ታላቁ ስምምነት እና አንድነት የአዲሱ ሰማይ እና የአዲሱ ምድር የክርስትና ራዕይ ጥልቅ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ቀውሶች ባሉባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ መታየታቸውን አብራርተው፥ ከሁለቱም የተወረሱ ወጎች ሰዎችን ባለመረጋጋት እና በለውጥ ውስጥ ለመምራት በሚያስችል የተስፋ አድማስ እንደገና መተርጎማቸውን አስረድተዋል።

በ ‘ኮንፊሺያን’ ባህል ውስጥ ያለ ታላቅ ስምምነት

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ በንግግራቸው እንደገለጹት፥ የ ‘ኮንፊሺያን’ አስተሳሰብ በኋላ ላይ ሁከት በነገሠባቸው የጦርነት ዘመናት ውስጥ በተከታዮቹ የተገነባውን አሳማኝ የሆነ ኅብረተሰብ ራዕይ ለመፈለግ ወደ ባሕላዊ ቅርስነት መዞሩን አስታውሰዋል። የአምልኮ ሥርዓቶች ዝግመተ ለውጥ ይህ የ“ታላቁ መንገድ (ዳኦ) ራዕይ ከሰማይ በታች ሲነግሥ” በሥነ-ምግባር እሴቶች፣ በፍትህ እና በጋራ ጥቅም የሚተዳደር ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም የዳቶንግ ሃሳብ በእርስ በርስ ግንኙነቶች፣ በኃላፊነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የማኅበራዊ-ሞራል እና የውበት አድማስ እንደሚሰጥ፣ ሰብዓዊ ደህንነት በጋራ አንድነት ላይ የተመሠረተ እርስ በርስ የተሳሰረ ማኅበረሰብ አድርጎ እንደሚገነዘብ ታውቋል።

በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸ "አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር"

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ የራእይ መጽሐፍን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ የፍጥሞስ ዮሐንስ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በሮማ ግዛት ተጽዕኖ ሥር ለሚኖሩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች በምሳሌያዊ አነጋገር፥ "ባቢሎን" ተብሎ የተመሰለው የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በማየት የእስራኤልን ትንቢታዊ ተስፋዎች በአዲስ ንባብ አማካኝነት የታደሰ ተስፋን እንደሰጣቸው አብራርተዋል።

በራእዩ መደምደሚያ ላይ ዮሐንስ እግዚአብሔር በሰው ልጆች መካከል የሚኖርበት፣ እንባውን ሁሉ የሚያብስበት እና ፍጥረትን በፍትህ፣ በሰላምና በኅብረት የሚያድስበት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” መምጣትን ማወጁን ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ አስረድተዋል።

ሁለቱ አስተሳሰቦች የሚገናኙበት ነጥቦች

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ በማብራሪያቸው፥ ምንም እንኳን በተለያዩ ባህሎች የተቀረጹ ቢሆንም ሁለቱም ራእዮች ተነሳሽነትን ማግኘታቸውን ገልጸው፥ ይህም እያንዳንዱን ወግ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ በመማማር እና በመገናኘት አብረው እንዲያድጉ ለማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።

የጋራ ሃሳባቸው ሲጠና ፉክክር፣ እኩልነት ማጣት እና ኢ-ፍትሐዊነት ባለበት ዘመን ውስጥ ሁለቱም ማለትም የክርስቲያኖች “የአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ተስፋ እና የኮንፊሽያውያን የዳቶንግ ቁርጠኝነት “መለያየት፣ ራስ ወዳድነት እና ጭቆና የማይቀር ነው” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ የሚያደርግ ብሩህ ተስፋ ያለው ራዕይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሃይማኖት መካከል የሚደረግ ውይይት ወሳኝ ምዕራፍ

ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ ይህ የመጀመሪያው የክርስቲያን እና የኮንፊሺያን ውይይት ለወደፊት ስብሰባዎች ሞዴል እንደሚሆን እና ከአካዳሚያዊ ልውውጥ የበለጠ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ዘላቂ የጓደኝነት እና የውይይት ጉዞ መጀመሪያ ምልክት ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፀሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢንዱኒል ጃናካራትኔ በበኩላቸው ውይይቱ በክርስቲያኖች እና በ ‘ኮንፊሺያን’ እምነቶች መካከል ባለው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ በመክፈት የጋራ ትምህርት እና በሰብዓዊ አገልግሎት ውስጥ ትብብር" እንደሚያሳድግ ገልጸው፥ “ይህም ለክርስቲያን እና ለ ‘ኮንፊሺያን’ ግንኙነቶች ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት መካከል ለሚደረገው ውይይት ጠቅላላ ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ለክርስቲያን-ኮንፊሽየስ የውይይት መመሪያዎች

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ካንካናማላጅ “አዲሱ ዘመናችን” የሚለውን የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድን ጠቅሰው እንደተናገሩት፥ “ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ሃይማኖቶች ውስጥ ያለውን እውነት እና ቅዱስ የሆነውን ነገር አትቃወምም” የሚለውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ልዩነቶችን ለማስወገድ ሳይሆን የጋራ መግባባትን ለማጎልበት፣ እርስ በርስ ለመማማር እና ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም ሲባል ጎን ለጎን ለመሥራት እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል የሚገኝ የሶጋንግ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ
በደቡብ ኮርያ መዲና ሴኡል የሚገኝ የሶጋንግ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ

 

 

05 Aug 2026, 16:07