ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን “ሰላም የሚጀምረው ለሌሎች ስቃይ በማዘን ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ረቡዕ ሐምሌ 29/2018 ዓ. ም. የሜክሲኮ ብሔራዊ የሰላም ውይይት ተወካዮች በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ሰላምን በማጎልበት ረገድ ያላቸውን ልምድ በቀጥታ ለመስማት መገናኘታቸውን የሜክሲኮ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መግለጫ አስታውስቋል።
ስብሰባው ምሁራንን፣ የሕዝብ ባለሥልጣናትን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የጠፉ ዘመዶቻቸውን የሚፈልጉ እናቶችን፣ የፖሊስ መኮንኖችን እና የንግድ መሪዎችን ጨምሮ ከሳን ሉዊስ ፖቶሲ፣ ከኦሃካ፣ ከኩዌሬታሮ፣ ከፑዌብላ፣ ከሜክሲኮ መንግሥት እና ከሜክሲኮ ከተማ የተውጣጡ ተወካዮችን ማሳተፉ ታውቋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ንግግር፥ “ሰላም የሚጀምረው ለሌሎች ስቃይ በማዘን ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ በሜክሲኮ ፑዌብላ ግዛት ውስጥ የጠፋ ልጇን የምትፈልግ እናት ምስክርነት ጠቅሰዋል። ሰላም በየቀኑ በትዕግስት የሚገነባ መሆኑን አስታውሰው፥ ተሳታፊዎቹ ተስፋ እንዳይቆርጡ በማበረታት፥ ይህ ተሞክሮ በዓመፅ ለተጠቁ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተነሳሽነት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
የሜክሲኮ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በበኩሉ፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሰላምን በመገንባት ረገድ በርካታ የትብብር ምሳሌዎችን መጋራታቸውን አስታውሷል። አንድ ምስክር በፑዌብላ ግዛት የሚወዷቸውን የጠፉ ሰዎችን በሚፈልጉ የቤተሰብ ድርጅቶች እና በሕዝብ ባለሥልጣናት መካከል የተደረገውን የጋራ ጥረት ገልጾ፥ ብሔራዊ የሰላም ውይይት ለሲቪክ እና ለፖለቲካ አመራር የስልጠና ቦታ መሆኑን አስረድቷል።
ከኤካቴፔክ የመጣ የፖሊስ መኰንንም እንዲሁ፥ ሰላምን ለማስፈን እና የማኅበረሰብ ፖሊስ ሞዴልን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ትብብር መኖሩን ተናግሯል። ከኳሬታሮ የተውጣጡ ተወካዮችም በበኩላቸው፥ ብሔራዊ የሰላም ውይይት መድረክ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች አንድ ለማድረግ እንደ ገመድ ማገልገሉን ገልጸዋል። ከኦሃካ የተውጣጡ ተወካዮች ብሔራዊ ውይይት በከፍተኛ አደጋ ላይ ባሉ አካባቢዎች ለሚያገለግሉ ካኅናት መጽናናት እና ድጋፍ እንደሰጠ አብራርተዋል። ከሳን ሉዊስ ፖቶሲ የመጡት ተወካይም ተጨማሪ ቁምስናዎች በሰላም ግንባታ ሥራ እንዲሳተፉ ለማበረታታት ያለውን ተግዳሮት ጠቅሰዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ብሔራዊ የሰላም ውይይት አባላትን በትኩረት ካዳመጡ በኋላ፥ በትዕግስት የሰላም ግንባታ ሥራ ለመጽናት በየቀኑ ለሚያደርጉ ጥረቶች ያላቸውን አጋርነት ገልጸው፥ ንቅናቄው በዓመፅ ለሚሰቃዩ በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የተስፋ ምንጭ መሆኑን እና የቅድስት መንበር ድጋፍ እንዳለው አረጋግጠዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ለሥራቸው እውቅና እና ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሰላምን ለመገንባት ባላቸው የጋራ ቁርጠኝነት እና ከእነርሱ ጋር ለመቀራረብ ላሳዩት ፍላጎት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።