ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር  

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር የሩሲያ ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ተገለጸ

በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሩሲያ ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በኤክስ ገጹ ላይ ይፋ ባደረገው መርሃ ግብር መሠረት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ለሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ ሩሲያ መድረሳቸውን ገልጾ፥ ዓላማውም በጋራ ውይይት እና በሰላም ላይ ያተኮረ እንደ ሆነ አስታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ሩሲያ ውስጥ ከአገሪቱ ባለስልጣናት፣ ከሞስኮ ፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች እና ከካቶሊክ ማኅበረሰብ ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሩሲያ ፌዴሬሽን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር ይፋ መሆኑን የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በኤክስ ገጽ ላይ አስታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ወደ ሞስኮ የሚደርሱት ዛሬ ነሐሴ 18 ሲሆን ወደ ሮም የሚመለሱት ዓርብ ነሐሴ 22/2018 ዓ. ም. መሆኑን የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ማክሰኞ ነሐሴ19 ከሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ከተገናኙ በኋላ ከሞስኮ ፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ከሆኑት አቡነ አንቶኒ ኦፍ ቮሎኮላምስክ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

በቀጣዩ ቀን ረቡዕ ነሐሴ 20/2018 ዓ. ም. ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጽሕፈት ቤት የፕሬዝዳንት ረዳት ከሆኑት ዩሪ ኡሻኮቭ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

የጊዜ ሰሌዳው በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ እንኳን ቅድስት መንበር የውይይት መንገድን ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ሐሙስ ነሐሴ 21/2018 ዓ. ም. ከካቶሊክ ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙ ሲሆን፥ የዕለቱን መርሃ ግብር የሚጀምሩት ከካህናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት ጋር በሚደረግ ስብሰባ እንደሚሆን ታውቋል።

ቀጥለውም በሞስኮ በሚገኘው እጅግ ንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

በሩሲያ የሚገኝ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ በቁጥር አነስተኛ ሲሆን በመልክአ ምድር አቀማመጥ ሰፊ በሆኑ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ተበታትኖ እንደሚገኝ ታውቋል።

ይህም በሞስኮ የሚገኘውን የወላዲተ አምላክ ሀገረ ስብከት፣ በሳራቶቭ የሚገኘውን የቅዱስ ክሌመንት ሀገረ ስብከት፣ በኖቮሲቢርስክ የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ግልጸት እና የኢርኩትስክ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያካትት ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ወደ ሩሲያ መዲና ሞስኮ ሲጓዙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ ሲታወቅ፥ የቅርብ ጊዜ ጉብኝታቸው የተካሄደው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በኅዳር ወር 2021 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በወቅቱ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካሂል ሚሹስቲን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ ሂላሪዮን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል።

 

24 Aug 2026, 15:42