ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ መግለጫ ሲሰጡ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ መግለጫ ሲሰጡ  (ANSA)

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር በሞስኮ ጉብኝታቸው የሩስያ እና ዩክሬይን ጦርነት እንዲያበቃ አሳሰቡ

በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሞስኮ በተካሄደው የሁለትዮሽ ስብሰባ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ተወያይተዋል። ውይይታቸው በዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና በሩሲያ ውስጥ ስላለው ካቶሊክ ማኅበረሰብ እንዲሁም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም ለመፍጠር በታለሙ ሰብዓዊ ተነሳሽነቶች ላይ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማክሰኞ ነሐሴ 19/2018 ዓ. ም. በሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ቢሮ በተካሄደው የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በዋና ዋና በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚገናኙባቸውን በርካታ ዘርፎች ለይተው በማውጣት በሩሲያ ፌዴሬሽን እና በቅድስት መንበር መካከል በመካሄድ ላይ ባለው ቀጣይ ውይይት አስፈላጊነት ላይ ተስማምተዋል።

ድርድሮች እና ሰብዓዊነት ቁርጠኝነት

ከአንድ ሰዓት በላይ በፈጀ ስብሰባቸው መጨረሻ ላይ በሞስኮ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ  የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጆቫኒ ዳኒየሎ ተገኝተዋል። በስብሰባቸው መጨረሻ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ መግለጫ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም እና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ እውነተኛ ድርድር እንዲጀመር የጠየቁትን ጥሪ ብጹዕነታቸው አስታውሰው፥ ቅድስት መንበር  በግልጽ አቋሟ “ግጭቱ በወታደራዊ ኃይል ሊፈታ አይችልም” ማለቷን ተናግረው፥ በመሆኑም ለፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሂደቶች ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ሩሲያ እና ዩክሬን ግልጽነትን እና ፈቃደኝነትን እንዲያሳዩ፥ በተለይም በሲቪሎች፣ በመሠረተ ልማት፣ በቁስለኞች እና የጦር እስረኞች ረገድ ዓለም አቀፍ እና የሰብዓዊነት ሕግን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“ጦርነቱ ይቁም!”

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በዩክሬን ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ “ጦርነት ማብቃት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል። በጦርነቱ ምክንያት በሁለቱም ወገኖች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር መጨመሩ እና የሕዝቡም ስቃይ መቀጠሉ ታውቋል።

“ላለፉት ስህተቶች እስረኛ አለመሆን እና ለወደፊት ግንኙነቶች ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣ ጦርነትን ማስቆም እና ጥላቻን ማስወገድ አጣዳፊ እና አስፈላጊ ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በድጋሚ ተናግረዋል።

በሩሲያ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ቅድስት መንበር ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ላሳየችው ዝግጁነት እና ለሰላም ላላት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸው፥ በሁለቱ መካከል የተካሄደው ስብሰባም “እጅግ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ከሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጋር ከግጭቱ ጋር በተያያዙ የሰብዓዊነት ጉዳዮች ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅድስት መንበር ለሰላም የሰጠችው ቁርጠኝነት

የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር “በሰብዓዊነት መስክ የሚታይ ማንኛውም ተጨባጭ ውጤት መከራን ለማስታገስ እና ግጭት ውስጥ በገቡ ወገኖች መካከል ያለውን ዝቅተኛ መተማመንን ወደ ነበረበት ለመመለስ ይረዳል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ በዚህ ረገድ የካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሩሲያ የሚያደርጉትን ተልዕኮ አስፈላጊነት አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ቅድስት መንበር ለውይይት ዕድል ማመቻቸት፣ የሰብዓዊ ጥረቶችን ለማጠናከር እና ሰላምን ለማምጣት የሚያግዙ አስተዋጽኦችን ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ገልጸዋል።

አብያተ ክርስቲያናት ሰላምን በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከሚኒስትር ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት ውይይት፥ አብያተ ክርስቲያናት እና የአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ለመርዳት እና እርቅን በመደገፍ ላይ ያላቸውን ጠቃሚ ሚና አስታውሰዋል።

በዚህ አውድ ውስጥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እና ፍላጎቶች በተለይም የቤተ ክርስቲያን እና የሃይማኖት ማኅበረሰቦች የሚያከናውኑትን የበጎ አድራጎት ተግባራት አጉልተው አሳይተዋል።

ከሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ጋር የተደረገ ውይይት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ማክሰኞ ምሽት ከሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ እና የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒን ጋር በክልላዊ ሁኔታ ላይ በመመሥረት በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንቶኒ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እና በቅድስት መንበር መካከል ባለው ቀጣይ ወዳጃዊ ግንኙነት መርካታቸውን ገልጸል።

 

 

26 Aug 2026, 16:49