ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሰገነት ላይ ንግግር ሲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሰገነት ላይ ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት ዘወትር የሐዋርያዊ እረኛ መልዕክት ነው!”

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት እና በአስተምህሮአቸው ሚና ላይ በማሰላሰል፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት ዘወትር የሐዋርያዊ እረኛ መልዕክት ነው!” በሚል ርዕሥ ያዘጋጀውን ርዕሠ አንቀጽ እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ ጦርነት እና ሰላም፣ ስለ ስደት ወይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን የሰው ልጅ ስብዕናውን ሳያጣ እንዴት መኖር እንደሚችል በሚናገሩበት ወቅት ዘወትር የሐዋርያ ጴጥሮስ ተተኪ እና ከሁሉም በላይ መንፈሳዊ መሪ በመሆን ነው።

የሮም ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1929 ዓ. ም. የሮማውያንን ጥያቄ በፈታው የላተራን ስምምነት መሠረት የዓለማችን ትንሿ እና ሉዓላዊ አገር፣ በጣሊያን መዲና ሮም ውስጥ በምትገኝ ትንሿ ቫቲካን ውስጥ ሆነው የሰው ልጆችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ፖለቲከኛ ወይም ስለ ፖለቲካ ይናገራሉ ማለት አይደለም።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 4/1965 ዓ. ም. ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ይህን በሚገባ አስረድተዋል፥ ‘ይህ ጉባኤ ሁላችሁም በሚገባ እንደምታውቁት ሁለት ዓይነት ባህሪ አለው። ቀላልነቱን እና ታላቅነቱን በአንድ ጊዜ የሚገልጽ ነው። ቀላልነቱን ስንመለከተው ለጉባኤው የሚናገረው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደ እናንተ ሰው እና ሉዓላዊ መንግሥታትን ከሚወክሉት መካከል እጅግ ትንሹ ወንድማችሁ በመሆን ነው። እኛን ከዚህ አንፃር መመልከትን ከመረጣችሁ ምሳሌያዊ እና ጊዜያዊ ሉዓላዊነት ብቻ ያለውን መንፈሳዊ ተልዕኮውን በነፃነት መጠቀሙን እና ከእርሱ ጋር መገናኘት ለሚፈልጉት ማረጋገጥ የምፈልገው ከዚህ ዓለም ሉዓላዊነት ነፃ መሆኑን ነው’ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በዩናይትድ ስቴትስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ላይ ስለራሳቸው ሲናገሩ፡- ‘ጊዜያዊ ኃይል የለውም፤ ከእናንተ ጋርም ለመወዳደር ምንም ፍላጎት የለውም፤ እንደ እውነቱ ከሆነ በምንችለው መስክ ሁሉ በትህትና እና በፍቅር ለማገልገል ከመፈለግ ሌላ ለጉባኤው የምናቀርበው ጉዳይም ጥያቄም የለንም’ ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልግል ያለውን ፍጹም ነፃነት ለማረጋገጥ ሲባል፥ ከአንድ ምዕተ ዓመት ገደማ በፊት የሮም ጳጳስ እና የኩላዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎቱን የሚፈጽምበትን ትንሽ መሬት ተገኝቶ ተቋቋመ። ነገር ግን ይህ ከሌላ ከማንኛውም መንግሥት የተለየ ፍላጎት እንዳለው በትክክል ለመለየት የተነደፈ ነበር። ይህ ንድፍ የሁለትዮሽ ተልዕኮ ማረጋገጫ አይደለም። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሀገር መሪነት ሚናን ማጉላት እና ማጋነን ወይም በዚህ ሚና አስፈላጊነት ላይ ማተኮር የሚያሳስት ነው። ምክንያቱም የዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ እረኛ እውነተኛ ተልዕኮ ዋጋን ያስከፍላል። ወንጌልን ለማወጅ ብቻ ዓላማ ያለው ሐዋርያዊ እረኛ ለካቶሊካዊ ምዕመናን፣ ለክርስቲያኖች፣ ለአማኞች እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ ከመሣሪያ ትጥቅ ነጻ የሆነ ሰላማዊ የፍቅር እና የወንድማማችነት መልዕክትን ይናገራል።

በዚህም የሚላን ከተማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት እና በቀድሞ ስማቸው ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሞንቲኒ በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 10/1962 ዓ. ም. በ‘ካምፒዶግሊዮ’ ባደረጉት ንግግር አፅንዖት ሰጥተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በዚያ ንግግራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ጊዜያዊ ኃይል በ1870 ዓ. ም. ማብቃቱን እና በጳጳሳዊ ግዛቶች ላይ የደረሰውን ውድቀት አስመልክተው ሲናገሩ፥ ‘የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አስተዳደር እና በዓለም ላይ ያላት የሞራል ተጽዕኖ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮን እና የወንጌል ምስክርነትን በልዩ ኃይል በጀመሩት ጊዜ ነበር’ ብለዋል።

የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሰው ልጅ ሕይወት በእያንዳንዱ ደረጃ መከበር እንዳለበት ጥሪ ሲያቀርቡ፥ የሕዝቦችን የጋራ ጥቅም በአእምሯቸው ይዘው ስለ ሰላም ሲናገሩ፣ ከ‘ፍትሃዊ ጦርነት’ ጽንሰ-ሃሳብ በላይ የጦር መሣሪያ ውድድር እንዲቆም፥ ማኅበራዊ አስተምህሮን ይፋ በማድረግ ውይይት እና ድርድር እንዲደረግ፣ የስደተኞች ሰብዓዊ ክብር ሳይዘነጋ በሄዱበት ሁሉ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ሲጠይቁ፣ ድሆችን የወንጌል እምብርት በማድረግ የበለጠ ፍትሃዊ እና ትክክለኛ ማኅበረሰብን መገንባት እንዳለብን ሲያስታውሱን፣ የሃይማኖት ነፃነት እንዲጠበቅ፣ ለፍጥረት እንክብካቤን በማድረግ ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን የማስተላለፍ አስፈላጊነትን ሲያስረዱን እንደ መንግሥት መሪ ሳይሆን ወንጌልን ለዓለም የሚያውጁ በመሆናቸው ብቻ ነው” ሲል ርዕሠ አንቀጹ ሐተታውን ደምድሟል።

14 Jul 2026, 16:56