የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለዓለም ስቃይ የእርዳታ እጅ መሆኑ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ወደ ስፔን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ የመጀመሪያ ቀን ላይ በማድሪድ የሚንቀሳቀሰው ‘ሲዲያ 24 ሆራስ’ በተሰኘው ማህበራዊ ፕሮጀክት መርሃ ግብር ላይ ለሰራተኞች እና ለተጠቃሚዎች ባደረጉት ንግግር፣ “የበጎ አድራጎት ተግባር ሊዘገይ አይገባም” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ እነዚህ ንግግሮች በቃላት ብቻ የቀሩ ሳይሆን፥ በተግባር መሬት ወርደው እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በህፃናት መጫወቻ አሻንጉሊት እና በክፍላቸው ግድግዳ ላይ በተለጠፈ የኦርቶዶክስ ካቴድራል ምስል የተከበቡት አንዲት እናት እና ሴት ልጇ በአነስተኛ መኝታ ክፍላቸው ውስጥ የብስኩት እሽግ እና የፓስታ ከረጢት ተሸክመው የሚያሳይ ምስል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዓለም ዙሪያ ለሚሰቃዩ ሰዎች የሚልኩትን የምግብ፣ የመድኃኒት እና የሰብአዊ እርዳታ ተግባር ያሳያል ተብሏል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን በበኩላቸው ከቫቲካን ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‘አንድነት ድንበር እንደሌለው እና በብሔርተኝነት እንደማይገደብ’ የገለጹ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው የእርዳታ ሥራዎች ‘መከራ እና አስቸኳይ ፍላጎት’ ባለበት ቦታ ሁሉ መድረስ እንዳለበት ጠቁመው፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት የድጋፍ ሥራው ፈጣን፣ ተግባራዊ እና በሚገባ የተቀናጀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ፥ በተለይም ለድሆች የቅዱስ አባታችንን ቅርበት እና ርህራሄ እንዲለማመዱ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበው፥ ቤተክርስቲያን በፍቅር የተሞላ አቀባበል በማድረግ አብራቸው በመጓዝ እና በመደገፍ ትቀጥላለች ብለዋል።
በቅድስት መንበር የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል የሚላከው የሰብዓዊ እርዳታ ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በጦርነት የተጎዳውን የዩክሬን ህዝብ እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ እና በሊባኖስ ውስጥ ያሉትን ተጎጂዎች ያለማቋረጥ መደገፉ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት ለዓመታት በዘለቀው ቀጣይነት ያለው አብሮነት ላይ በመመስረት እና ለእርዳታ የሚቀርቡ ጥሪዎች በሚነሱበት ጊዜ ሁሉ በፍጥነት ምላሽ በመስጠት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሁሉም አህጉራት መጽናናትን መስጠታቸውን እንደቀጠሉ ተነግሯል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የበጎ አድራጎት አገልግሎት መልክዓ ምድር ሳይገድበው ከአውሮፓ እና ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ኢስያ፣ እንዲሁም አፍሪካ እና አሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ያለማቋረጥ እና ያለ ልዩነት እንደሚደርስ የተነገረ ሲሆን፥ በመሬት መንቀጥቀጥ እና በአውሎ ነፋሶች፣ በድርቅ እና በጎርፍ የተጎዱትን ብቻ ሳይሆን፥ በዕለት ተዕለት ግጭት፣ በተተው ህፃናት እና በቂ ምግብ ለማግኘት ለሚታገሉ ቤተሰቦችም ጭምር ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በአውሮፓ ውስጥ እንግዳ ተቀባይ መሆን
አብዛኛውን ጊዜ የበለጸገች ተብላ በምትገለጸው የአውሮፓ አህጉር ውስጥ እንኳን ሳይቀር የድህነት እና የመገለል ታሪኮች እንደሚስተዋሉ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በሜዲትራኒያን የስደተኞች መጓጓዣ መስመሮች መገናኛ በሆነችው የቆጵሮስ ደሴት ቅድስት መንበር በመቀበያ ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ ጥገኝነት ፈላጊዎች ምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና የስነ-ልቦና ድጋፍ የሚያቀርበውን የሳንት ኤጂዲዮ ፕሮጀክት እንደምትደግፍ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በምሥራቅ አውሮፓ በምትገኘው ጆርጂያ፣ በትብሊሲ ከተማ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ወጣቶች የሚሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማጠናቀቅ እርዳታ የሚሰጥ ሲሆን፥ ይህ ፕሮጀክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በግል ተሳትፈውበት የነበረ እና በአሁኑ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ፍጻሜ እያደረሱት ያለ ፕሮጀክት መሆኑ ተነግሯል።
ለመካከለኛው ምስራቅ እና ኢስያ እፎይታን ማምጣት
ከጋዜጣ አርዕስቶች ቢጠፋም ከሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ግን እንዳልጠፋ በሚነገርለት የሶሪያ ጦርነት ምክንያት በአከባቢው የሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች የተለያዩ ጫናዎችን እና ድምፅ አልባ ዛቻዎችን እየተጋፈጡ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በሶሪያ የቅድስት መንበር ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ሉዊጂ ሮቤርቶ ኮና እንደተናገሩት በቅርቡ ሩዝ፣ ጥራጥሬ እና የምግብ ማብሰያ ዘይት የያዙ 2,000 የምግብ ጥቅሎች በአከባቢው ለሚገኙ ቤተሰቦች እንደሚከፋፈሉ ይፋ አድርገዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የበጎ አድራጎት ሥራ ባንግላዲሽ ውስጥ በሚገኘው፣ በዓለም ላይ ትልቁ የስደተኞች ካምፕ በሆነው እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሮሂንጊያ ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ሃገር አልባ ሆነው በሚኖሩበት ‘ኮክስ ባዛር’ ካምፕ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ቀጣይነት ያለው የድጋፍ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅርቡ በዚያ ሰፊ ካምፕ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ መላካቸው ይታወሳል።
ከዚህም ባሻገር በቅርቡ በከባድ የጎርፍ አደጋ ለተጎዳው የቻቶግራም ሀገረ ስብከት የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለማከፋፈል፣ የግብርና እንቅስቃሴዎችን ወደነበረበት ለመመለስ፣ የምግብ ዋስትና ተነሳሽነቶችን ለመደገፍ፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለወላጅ አልባ ሕፃናት ድጋፍ እና በአደጋው ለተጎዱ መኖሪያ ቤቶች ጥገና ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
ይህ የቅድስት መንበር ተግባራዊ ድጋፍ ጋዛ እና ሊባኖስ ድረስ እንደሚዘልቅ የተነገረ ሲሆን፥ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በአካባቢው በሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ በኩል በጦርነቱ ለተዳከሙ ህዝቦች 15,000 የሚያህሉ አስፈላጊ መድኃኒቶች፣ የደም ግፊት መከላከያ መድኃኒቶች እና የህመም ማስታገሻዎችን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
አፍሪካ እንድታገግም የተደረገ ድጋፍ
ምናልባትም የሮም ጳጳስ በጎ አድራጎት ድርጅት ለአፍሪካ ያደረገውን ያክል በዬትኛውም ክልል አድርጎ እንደማያውቅ የሚነገር ሲሆን፥ በቡርኪናፋሶ፣ የኡሃጎያ ሀገረ ስብከት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ለእናቶች እና ለህፃናት ጤና ልዩ ትኩረት በመስጠት የተፈናቀሉ እና በድህነት የሚኖሩ ሰዎችን የሚያግዝ የጤና አጠባበቅ ፕሮጀክት ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
በቅድስት መንበር የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል በኬንያ ለሚገኘው የቅድስት አንጄላ ኢምቡ የህፃናት እንክብካቤ ማዕከል የተደረገው እርዳታ የተተው እና በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን በእጅጉ የረዳ ሲሆን፥ በዚህ ማዕከል ውስጥ ህፃናቱ ጥበቃ፣ መደበኛ የሆነ ምግብ እና ትምህርት እንደሚያገኙ ተገልጿል።
በማዳጋስካር፣ የካቲት ወር ውስጥ በተከሰተው አውሎ ነፋስ ምክንያት ከደረሰው ውድመት በኋላ፣ የቶማሲና ሃገረ ስብከት እርዳታ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የበጎ አድራጎት ፈንድ ከአስቸኳይ የምግብ ስርጭት ጀምሮ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ እስከ መገንባት እና የኑሮ መተዳደሪያን ወደነበረበት እስከ መመለስ ድረስ ያለ ዘርፈ ብዙ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በሌላ በኩል በዛምቢያ፣ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የተከሰተው ከባድ ድርቅ ሰብሎችን ማውደሙን እና በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች ለረሃብ መጋለጣቸውን ተከትሎ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጎ አድራጎት ድርጅት አባት ልጆቹን እንደሚንከባከብ ሁሉ ለእነዚህ ወገኖች እንክብካቤ ማድረጉ ተገልጿል።
በአሜሪካ አህጉራት የተደረጉ የድጋፍ ሥራዎች
ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የእርዳታ እጅ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች መድረሱን የቀጠለ ሲሆን፥ በአርጀንቲና የቱኩማን ሀገረ ስብከት ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ የተከሰተው ከባድ አውሎ ነፋስ ወደ 450 የሚጠጉ ተጋላጭ ህፃናትን እና ወጣቶችን የሚያገለግለውን ማዕከል የመመገቢያ አዳራሽ እና የሙያ ማሰልጠኛ ዎርክሾፖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ይታወቃል።
ይሄንን ተከትሎ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል በአስቸኳይ የተላከው የገንዘብ ድጋፍ የመልሶ ግንባታ ሥራው እንዲጀመር ማስቻሉ ተመላክቷል።
ከዚህም ባሻገር ማህበራዊ አለመረጋጋት እና የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት የአብዛኛውን የሃገሪቱ ህዝብ ዕለታዊ ኑሮን እጅግ አስቸጋሪ ባደረጉበት ሄይቲ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እርዳታ የምግብ አቅርቦት እንዲሁም የህክምና እና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፎችን በማድረግ ለተቸገሩ ቤተሰቦች እፎይታን መስጠቱ የተነገረ ሲሆን፥ በተመሳሳይ መልኩ በቬንዙዌላ በቅርቡ የተከሰተውን አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ተከትሎ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የበጎ አድራጎት ተቋም በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
በሃገሪቱ አደጋው እንደተከሰተ ወዲያውኑ ከተላከው የመጀመሪያ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በተጨማሪ፥ ዘላቂ የሆነ የመልሶ ግንባታ ሥራን ለመደገፍ ተጨማሪ እርዳታዎች መደረጋቸው ተነግሯል።
ከፍላጎቱ ባሻገር፣ መንስኤዎቹን መረዳት
“የበጎ አድራጎት ሥራ በአፋጣኝ እርዳታ ብቻ አያበቃም” ያሉት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የበጎ አድራጎት ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ሉዊስ እንደተናገሩት ማግለልን እና ስቃይን የሚያስከትሉትንና በኃጢአት ላይ የተመሰረቱ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን ለመለወጥ እንዲቻል የድህነት መንስኤዎችን ለይቶ ማወቅ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በመጨረሻም የቅድስት መንበር የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት “ፍቅር የክርስቲያናዊ ሕይወት ቁልፍ ነው” የሚለውን ግንዛቤ በሕያውነት ለማቆየት እንደሚሻ አስታውሰው፥ ለወንጌል ምላሽ በመስጠት የሚገለጸው የቸርነት ተግባር አስቸኳይነት፣ እንደ ቤተክርስቲያን ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር በመቀራረብ፤ መከራዎቻቸውንም ሆነ ተስፋዎቻቸውን በመጋራት እንድንኖር በየቀኑ ያነሳሳናል በማለት አጠቃለዋል።