የብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በ2027 ለሚካሄዱ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ‘ሪኮሌክቲንግ’ የተሰኘ መመሪያ ማሳተሙ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሲኖዶሱ ዋና ጽሕፈት ቤት፣ የሲኖዶሱን የአፈጻጸም ሂደት የአካባቢ ደረጃን የሚያጠናቅቁትን የግምገማ ጉባኤዎች ለማዘጋጀት እንዲያግዙ ለሀገረ ስብከቶች እና በምስራቃዊ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ሀገረ ስብከት ልርሚታዩት ለሃዋሪያዊ አስተዳደሮች የሚያገለግል አዲስ መመሪያ ያሳተመ ሲሆን፥ “ማስታወስ/ማሰላሰል፡ የአካባቢ ቤተክርስቲያንን የግምገማ ጉባኤ ዝግጅት መደገፍ” (Recollecting: Accompanying the preparation of the local Church’s evaluation Assembly) በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ይህ ሰነድ ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ መደረጉ እና በተለያዩ ቋንቋዎችም መዘጋጀቱ ተገልጿል።
“ግምገማ ማለት ቴክኒካዊ ሂደት ብቻ ሳይሆን የምስጋና እና የእውነት ተሞክሮ ነው” ያሉት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፥ አክለውም ‘ማስታወስ ወይም ማሰላሰል ማለት እግዚያብሄር በማህበረሰባችን ጉዞ ውስጥ ወደ ብስለት ያደረሳቸውን ነገሮች መለየት እና ወደ ቀጣዮቹ እርምጃዎች እንድንመራ የመፍቀድ ሂደት ማለት’ እንደሆነ ገልጸዋል።
የእግዚአብሔርን ተግባር ማስታወስ
ሰነዱ እንደሚያብራራው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማስታወስ ማለት ወደኋላ መመልከት ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም የአሁኑን ጊዜ ለመረዳት እና ለመጪው ጊዜ ለመዘጋጀት በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን ተግባር መለየትን የሚያመላክት ሲሆን፥ ስለሆነም፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሲኖዶሱን የአፈጻጸም ሂደት በምስጋና እና በቅንነት እንዲያጤኑት፣ እንዲሁም ለተግባር የደረሱ ሃሳቦችን እና የተጠሩባቸውን ቀጣይ እርምጃዎች እንዲለዩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ይህ መመሪያ በዋናነት ለሂደቱ ኃላፊነት ላለባቸው ብፁዓን ጳጳሳት እና ሃዋሪያዊ አስተዳደሮች እንዲሁም ሂደቱን ለሚያንቀሳቅሱት የሲኖዶስ ቡድኖች የተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሰነዱ አንድ የተወሰነ አሰራርን ብቻ የሚያስገድድ ሳይሆን፤ ይልቁንም ለእያንዳንዱ አካባቢ ሁኔታ ሊስማሙ የሚችሉ ጥያቄዎችን፣ መስፈርቶችን እና ተግባራዊ ምክሮችን እንደሚያቀርብ ተነግሯል።
እንደ ሰነዱ ገለጻ፣ ይህ አካሄድ ነፍስሄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሲኖዶሳዊነትን "ከውይይት የሚወለድ፣ በማዳመጥ የሚያድግ እና በማስተዋል የሚበስል መንፈሳዊ አኗኗር" ሲሉ የገለጹትን መርህ ያንፀባርቃል ተብሏል።
ከትውስታ ወደ ማስተዋል
መመሪያ ሰነዱ በሁለት በቅርበት የተያያዙ ክፍሎች የተከፈለ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የመጀመሪያው እያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ትዝታዎችንና ምስክርነቶችን በመሰብሰብ፣ “ምልክቶችን” በማወቅና በማዳመጥ እንዲሁም በሲኖዶሱ የመጨረሻ ሰነድ ውስጥ በተለዩት ሦስቱ የመለወጥ ሂደቶች ማለትም በግንኙነቶች፣ በቤተክርስቲያን ሂደቶች እና በትስስር አማካኝነት የለውጥ ሂደቶችን በመለየት ግልጽ ሪፖርት በማዘጋጀት እንደሚመራ ተገልጿል።
ሁለተኛው ክፍል በጳጳሱ የተጠራውን የግምገማ ጉባኤ ዝግጅትና አከባበር የሚመለከት ሲሆን፥ ይህም በጸሎት፣ በዝምታ፣ በጋራ ማሰላሰል እና በመንፈስ ውስጥ በሚደረግ ውይይት የሚገለጽ፣ እጅግ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ተሞክሮ እንደሆነ ተነግሯል።
ጉባኤው ግልጽ የሆነ በትረካ መልክ የተሰናዳ ሪፖርት እና ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ደብዳቤ የሚያዘጋጅ ሲሆን፥ ደብዳቤው በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን “የኅብረት ደብዳቤዎች” ላይ በመመርኮዝ የአካባቢው ቤተክርስቲያን የተረዳችውን፣ ልትወስዳቸው ያሰበችውን እርምጃ እና ለሌሎች ማህበረሰቦች የሚሆን የተስፋ መልዕክት እንደሚያካፍል ተገልጿል።
በቫቲካን በሚካሄደው ወደ 2028ቱ የቤተክርስቲያን ጉባኤ
ሁለቱም ጽሑፎች በጳጳሱ አንዴ ከፀደቁ በኋላ፣ ወደ ብሔራዊ ወይም ክልላዊ የሲኖዳል ቡድን መላክ እና እስከ ሰኔ 23 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ለሲኖዶሱ ዋና ጽሕፈት ቤት መጋራት እንዳለባቸው ጭምር ተገልጿል።
የብፁዓ ጳጳሳት ጉባኤዎች እና የምስራቅ ካቶሊክ ተዋረዳዊ መዋቅሮች እ.አ.አ. በ 2027 ዓ.ም. ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የሚካሄዱ ሲሆን፥ በ 2028 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ደግሞ አህጉራዊ ጉባኤዎች እንደሚካሄዱ እና ሂደቱ ጥቅምት ወር 2028 ዓ.ም. በቫቲካን በሚካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።