ፈልግ

VATICAN POPE LEO

“የፍቅር ደስታ” በተሰኘ ሐዋርያዊ ሠነድ ላይ ለሚደረግ ስብሰባ የዝግጅት ሠነድ መታተሙ ተገለጸ

ቫቲካን በጥቅምት ወር 2019 ዓ. ም. “አሞሪስ ላቲቲያ” ወይም (የፍቅር ደስታ) በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ለሚደረግ ስብሰባ ዝግጅት የሚሆን ሠነድ ማሳተሙ ታውቋል። ሠነዱ የታተመው ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ቤተሰብ የሰጡት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር የታተመበት አሥረኛ ዓመት ምንያት በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ያሳተሙት ሠነዱ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የተጠራውን ስብሰባ የሚመራ የዝግጅት ሠነድ ሲሆን፥ ይህም በቫቲካን ውስት ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 4/2019 ዓ. ም. ድረስ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስብሰባው እንደሚካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩት መጋቢት 10/2018 ዓ. ም. በጻፉት መልዕክት ላይ ሲሆን ይህም “የፍቅር ደስታ” የተሰኘ የድኅረ ሲኖዶሱ ሐዋርያዊ ምክር አሥረኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

የቤተሰብን ሕይወት በጥልቅ የሚጎዱ ለውጦች መኖራቸውን የተረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥  “በአሁኑ ወቅት በአካባቢያዊ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ግምት ውስጥ በማስገባት ሐዋርያዊ ሠነዱ በአሁኑ ጊዜ ለቤተሰቦች ወንጌልን ለማወጅ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ የጋራ መደማመጥ እና ሲኖዶሳዊ ማስተዋል ሊኖር እንደሚገባ በመፈለጉ ነው” ብለዋል።

በቅርቡ ሰኔ 20/2018 ዓ. ም. በተካሄደው ልዩ የመላው ካርዲናሎች ስብሰባ መደምደሚያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ቤተሰብ ጭብጥ በመመለስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ቤተሰብ ሲታገዝ እና እንክብካቤ ሲደረግለት የእርስ በርስ ግንኙነት፣ የአንድነት እና የተስፋ ትምህርት ቤት ያድጋል፤ ነገር ግን ሲቆስል ወይም ሲገለል ውጤቱን መላው ኅብረተሰብ ይሸከመዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በርካታ ቤተሰቦች ስብሰባውን እንደሚካፈሉ እና የሕይወት ልምዳቸውን እንደሚጋሩ ቅዱስነታቸው አስታውቀው፥ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ጳጳሳት ሮም ውስጥ በሚቀረቡ ጭብጦች ላይ በመሳተፍ እርስ በእርስ በጥሞና እንዲደማመጡ ጋብዘው፥ ወደ አካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያናት ሲመለሱ ከቤተሰቦች ጋር በመሆን ለቤተሰብ፣ ለሰው ልጅ ሕይወት እና ለጋብቻ ጥሪ ያላቸውን የጋራ ሐዋርያዊ ቁርጠኝነት ማደስ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የስብሰባው ቀናት ለእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለመደማመጥ እና ለማስተዋል እውነተኛ ሥፍራ እንዲሆኑ የታሰቡ እንደሆኑ፥ የቤተሰብን የሕይወት ተሞክሮ ለመቀበል፣ ተጨባጭ የሕይወት ታሪኮችን ለመጋራት፣ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ከቤተሰቦች ሕየወት ጋር በሚያጅቡ ሐዋርያዊ ተነሳሽነት ላይ ለማሰላሰል እና ከባለሙያዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ምቹ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከስብሰባው በፊት ባሉት ወራት ውስጥ በታቀዱት ጭብጦች ላይ ማሰላሰል እንዲጀምሩ የተጋበዙ ሲሆን፥ ይህም የአካባቢያቸውን አብያተ ክርስቲያናት ቤተሰቦችን በማዳመጥ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ታውቋል።

ይህ እጅግ ጥሩ የሆነ የሐዋርያዊ እረኝነት ጉዞ ቤተሰቦችን ማዕከል ያደረገ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን የሐዋርያዊ እረኝነት እንክብካቤ ተቀባዮች ብቻ ሳይሆኑ ቅዱስ ወንጌልን በዕለት ተዕለት ግንኙነቶች፣ ምርጫዎች፣ ጥረቶች እና ተስፋዎች ውስጥ ለተልዕኮዋ ንቁ ተገዢዎች አድርጎ እንደሚያስቀምጥ ታውቋል።

ስብሰባው የጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ ባይሆንም በሲኖዶሳዊ ዘይቤ እንደሚካሄድ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመላው የካርዲናሎች ጉባኤ መደምደሚያ ላይ እንደገለጹት፥ የሲኖዶሱን የአፈጻጸም ሂደት መንፈስ የሚጋራ በመሆኑ በመደማመጥ፣ በጸሎት እና በማስተዋል እንደሚካሄድ ታውቋል።

ለስብሰባው ዝግጅት የሚሆኑ እና ለአስተንትኖ የቀረቡት ጭብጦቹ አምስት ሲሆኑ እነርሱም፥ የዛሬው ቤተሰቦች እውነታ፣ ውበት እና ፈተና፣ የዘመናችንን ምልክቶች በቤተሰቦች ልምድ እና በቤተ ክርስቲያን የእረኝነት ቁርጠኝነት መለየት፤ ወጣቶች እና የጋብቻ ጥሪ፥ ወጣቶችን ማዳመጥ እና የጋብቻን ታላቅነት ለማሳወቅ አብረዋቸው መጓዝ፤ የጋብቻ ሕይወት ወሳኝ ጊዜ የሆኑ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እና በእያንዳንዱ የሕይወት ደረጃ ጥንዶችን ማዳመጥ እና መንከባከብ፣ በችግሮች ውስጥ አብሮ መጓዝ እና መደገፍ፣ ውስብስብ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ከቤተሰቦች ጋር መሆን፤ ክርስቲያን ቤተሰቦች ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ተገዢዎች በመሆን የትዳር ጓደኛ እና የቤተሰብ ፍቅርን ለተልዕኮ እንደ ማበረታቻነት መቀበል የሚሉ እንደሆኑ ታውቋል።

 

08 Jul 2026, 16:22