ር.ሊ.ጳ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሾሙ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሊቀ ጳጳሳት ክሪስቶፌ-ዛኪያ ኤል-ካሲስን በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ አድርገው ሾመዋል፣ እዚያም በተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት ቅድስት መንበርን ይወክላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ሹመቱ ቅዳሜ ዕለት ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም በቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ይፋ ተደርጓል። የሮዜል ልዩ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ሊባኖሳዊው ሊቀ ጳጳስ ኤል-ካሲስ እስከ አሁን ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና የመን የቫቲካን ሐዋርያዊ ልዑክ፣ እንዲሁም በአረቢያ ባሕረ ስላጤ ሐዋርያዊ ልዑክ ሆነው አገልግለዋል።
እ.አ.አ በ1994 ዓ.ም ሲመተ ክህነት ተቀብለው የነበረ ሲሆን እናም በ2000 ዓ.ም በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ጀምረው በኢንዶኔዥያ፣ በሱዳን፣ በቱርክ እና በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ሰርተዋል።
ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግሥታት ቋሚ ታዛቢነት ደረጃን በመያዝ በጠቅላላ ጉባኤው እና በሌሎች የተባበሩት መንግስታት አካላት ሥራ ላይ እንዲሳተፍ የአሁኑ ሹመት ያስችላቸዋል።
27 Jul 2026, 15:17