ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ለታዳሚዎች ሰላምታ ሲሰጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ለታዳሚዎች ሰላምታ ሲሰጡ  (@Vatican Media)

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ተልዕኮ መደገፊያ 54.5 ሚሊዮን ዩሮ መሰብሰቡ ተገለጸ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 2025 ዓመታዊ ሪፖርት እንደገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያካሂዷቸውን ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለ74 አገራት የሚሰጡትን ዕርዳታ መደገፊያ የሚሆን 59.8 ሚሊዮን ዩሮ መሰብሰቡ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በኩል የተሰበሰበው የ 2025 ዓ. ም. የገንዘብ መጠን 57.6 ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነ እና ወጪ የተደረገ የገንዘብ መጠን 59.8 ሚሊዮን ዩሮ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል።

በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በኩል የሚሰበሰብ የገንዘብ ድጋፍ እና መባዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለማስቀጠል እና እጅግ የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ የወጠኗቸውን በርካታ እቅዶችን ለማገዝ መሆኑን ሪፖርቱ አብራርቷል።

ምንም እንኳን ለድጋፍ የወጣው የገንዘብ መጠን ከገቢው በ2.2 ሚሊዮን ዩሮ የሚበልጥ ቢሆንም ልዩነቱ የተከሰተው የምንዛሪ ተመን መዋዠቅ ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

በሰዎች ልገሳ የተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መጠን 54.5 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፥ በሦስት ዋና ዋና ምንጮች እነርሱም በቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ክብረ በዓል ዕለት ከሀገረ ስብከቶች የተሰበሰበ፣ ከመባዎች እና ከውርስ የተገኙ ድጋፎች እንደሆነ ታውቋል።

ከፍተኛ ድጋፍ የተሰበሰበው ከሀገረ ስብከቶች ሲሆን ይህም 34.7 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ከጠቅላላው 63.6 በመቶ መሆኑ ታውቋል። ከግል ለጋሾች 5.4 ሚሊዮን ዩሮ፣ ከፋውንዴሽኖች 13 ሚሊዮን ዩሮ እና ከሃይማኖት ተቋማት 1.4 ሚሊዮን ዩሮ መሰብሰቡ ታውቋል።

ከሀገረ ስብከቶች እና በግለሰቦች ከተደረጉ ልገሳዎች መካከል ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛውን መጠን ማለትም 14.2 ሚሊዮን ዩሮ በማሰባሰብ ቀዳሚዋ ስትሆን፥ ጣሊያን 3.1 ሚሊዮን ዩሮ እና ብራዚል 2.1 ሚሊዮን ዩሮ መሰብሰቧ ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ ተልዕኮ መደገፍ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በኩል የተገኘ ጠቅላላ ድምር 54.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደ ነበር ተገልጿል። ከዚህም ውስጥ 41.2 ሚሊዮን ዩሮ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለማስቀጠል እና የቅድስት መንበርን ተግባራት ለመደገፍ የተመደበ ሲሆን፥ 13.3 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ የተቸገሩ ሰዎችን ለሚረዱ ፕሮጀክቶች የታሰበ እንደ ነበር ታውቋል።

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፥ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ከመደገፍ ጋር የተያያዙ ወጪዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. 404.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደ ነበሩ እና ከዚህም ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ 10 በመቶውን እንደሸፈን ታውቋል።

እነዚህ ልገሳዎች በችግር ውስጥ የሚገኙ የየአገራቱን ቤተ ክርስቲያናት ለመደገፍ እና በተወሰኑ አውዶች ውስጥ ለወንጌል አገልግሎት፣ ለአምልኮ፣ ለመልዕክት ስርጭት፣ ለሐዋርያዊ እንደራሴዎች፣ ለበጎ አድራጎት አገልግሎት፣ የታሪካዊ ቅርስ ጥበቃ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሰው ልጅ ልማት፣ ትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል እንዲሁም ከሕይወት እና ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ተነሳሽነቶችን እንደሚያካትቱ ታውቋል።

በ74 አገራት ውስጥ የተከናወኑ ፕሮጀክቶች

የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በ74 አገራት ውስጥ 252 ቀጥተኛ የዕርዳታ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ በድምሩ 13.3 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ያደረገ ሲሆን፥ ፕሮጀክቶቹ በሦስት ዘርፎች እነርሱም የወንጌል ሥርጭትን ማስቀጠል፣ ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ለወንጌል ስርጭት የሚደረገውን የድጋፍ መጠን ማሳደግ መሆናቸው ታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉ ቤተ ክርስቲያናትን፣ ገዳማትን፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማዕከላትን፣ የመማሪያ ክፍሎች እና ትምህርት ቤቶች ግንባታን፥ እንዲሁም ለጋዛ ነዋሪዎች የሚደረግ ዕርዳታን፣ ለአካባቢ ማኅበረሰቦች የሚደረግ ድጋፍ እና በሚስዮን አገራት እና አስቸኳይ ድጋፍን በሚጠይቁ አካባቢዎች ለሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት የሚደረገውን ድጋፍን ያካትታል።

ከፍተኛውን የዕርዳታ መጠን የምታገኝ አፍሪካ ስትሆን በአኅጉሪቱ የተወጠኑ 73 ፕሮጀክቶችን ለማስኬድ 5.2 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡ ታውቋል። እስያ 3 ሚሊዮን ዩሮ፣ አውሮፓ 2.6 ሚሊዮን ዩሮ፣ ሰሜን አሜሪካ 2.4 ሚሊዮን ዩሮ እና ኦሽንያ 100,000 ዩሮ ማግኘቷ ታውቋል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከእስያ የሚመጡ ካኅናት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ ለማስቻል  በርካታ የትምህርት ዕድሎች እንደተሰጡ እና ለዩክሬን ሕዝብም የሰብዓዊ ዕርዳታ መደረጉን ገልጿል።

ሪፖርቱ በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “በውይይት እና በእርስ በርስ ግንኙነት አማካይነት የመገናኛ ድልድይን ለመገንባት እና እንደ አንድ ሕዝብ አንድ ላይ በመሆን ዘወትር በሰላም ለመኖር እርዱን” በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በመጥቀስ ተጠናቅቋል።

 

01 Jul 2026, 16:18