የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ  (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር ለኤድስ ሕሙማን የሚደረግ እንክብካቤ እና መከላከያው ተጠቂዎችን በሙሉ ሊደርስ ይገባል አለች

ቅድስት መንበር በተባበሩት መንግሥታት በተካሄደው ከፍተኛ የኤችአይቪ/ኤድስ ስብሰባ ላይ ባስተላለፈችው መልዕክት፥ በሽታውን በመዋጋት ረገድ የተገኘውን ዕድገት በመግለጽ፥ በተለይም ሕጻናት እና ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ሕክምናው እንዲደርሳቸው የበለጠ ጥረት እንዲደረግ አሳስባለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር የኤድስ በሽታን ለማስቆም የሚደረግ ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነትን እንደገና እንዲታደስ በማሳሰብ፥ ኤችአይቪን በመከላከል እና በማከም ረገድ የተገኘውን ውጤት በደስታ ተቀብላ ነገር ግን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ብዙ ሰዎች አሁንም የሕይወት አድን እንክብካቤ እንደሌላቸው አፅንዖት ሰጥታለች።

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ዓርብ ሐምሌ 3/2018 ዓ. ም. በተካሄደው የኤችአይቪ/ኤድስ ከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ ላይ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ተልዕኮ የተሳተፈ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2010 ዓ. ም. ጀምሮ በአብዛኛዎቹ ክልሎች አዳዲስ የኤችአይቪ ስርጭት መቀነሱን እና ሰፊ የፀረ-ኤችአይቪ ሕክምና ተደራሽነት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ረጅም እና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻሉን ገልጿል።

ለሁሉም ሰው ወጥ እንክብካቤ መደረጉን ማረጋገጥ

ልዑካኑ በጤና ሥርዓቶች፣ በሕክምና ምርምር እና በአካባቢው የመድኃኒት ምርት ላይ ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እና ለሁሉም ሰው ወጥ የሆነ እንክብካቤ እንደሚደረግ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የልኡካን ቡድኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን መልዕክት ጠቅሶ እንደተናገረው፥ ቅድስት መንበር በኅብረተሰቡ የተገለሉትን ችላ ማለት እንደማይገባ ማስጠንቀቋን አስታውሶ፥ “በጤና አገልግሎት ላይ በተሳሳቱ አፈ ታሪኮች ላይ በመመርኮዝ በርካታ የድህነት እና የተጋላጭነት ሁኔታዎችን ችላ የሚባለውን ማኅበረሰብን መዘንጋት አንችልም” ብለዋል።

በተለይ ለልጆች አፅንዖት የሰጠው መግለጫው፥ ምንም እንኳን ከኤችአይቪ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ሦስት በመቶ የሚሆኑትን ብቻ የሚይዛቸው ቢሆንም፥ በምርመራ እና በሕክምና ውስጥ በሚታየው ዘላቂ ክፍተቶች ምክንያት ከኤችአይቪ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚሞቱት የሕጻናት ቁጥር አሥራ ሁለት በመቶ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ለእናቶች ጥራት ያለው የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድኅረ ወሊድ እንክብካቤ እንዲደረግ፣ ከኤችአይቪ ጋር ለሚኖሩ ሕጻናት ውጤቶችን ለማሻሻል ቅድመ ምርመራ እና ተስማሚ የሆኑ መድሃኒቶች አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥቷል።

የቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነት

ቅድስት መንበር በመጨረሻም፥ ቤተ ክርስቲያን በበሽታው ለተጎዱ ሰዎች እንክብካቤ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለች።

“በዓለም ዙሪያ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ እንክብካቤን የሚያቀርቡት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጤና አጠባበቅ ተቋማት፥ ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ የሚሰጥ እንክብካቤ ከሰብዓዊ ክብር ጋር በሚስማማ መልኩ ሕክምና እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይቀጥላሉ” ሲሉ ልዑካኑ ተናግረዋል።

 

13 Jul 2026, 16:48