ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በበርዲቺቭ በነበራቸው ቆይታ በእመቤታችን ቀርመሌዎስ ቤተመቅደስ ተገኝተው በሃገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት ማድረጋቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከኪየቭ በስተደቡብ ምዕራብ፣ በመኪና የሁለት ሰዓት ያህል መንገድ ላይ በምትገኘው በርዲቺቭ ከተማ በዩክሬን ውስጥ የላቲን ሥርዓት ተከታይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ወደነበሩበት የተመለሱበትን 35ኛ ዓመት ለማክበር ከ3,000 በላይ ሰዎች በቀርመሌዎስ ቤተ መቅደስ ግቢ ውስጥ የተሰበሰቡ ሲሆን፥ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ውጭ በተደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ቤተሰቦች፣ ህፃናት እና ወጣቶች እንዲሁም በርካታ አረጋውያን እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በደስታ ተሞልተው በስፍራው መገኘታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዓሉ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ሰማዩ በከባድ ደመና ተሸፍኖ ዝናብ መዝነቡ ቢነገርም፤ ሆኖም መጥፎው የአየር ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተወገደ፣ በመጨረሻም ለዚያ አካባቢ ያልተለመደ ሞቅ ያለ የፀሐይ ብርሃን መታየቱ ተነግሯል።
በርዲቺቭ በዩክሬን እና ከዚያም ባሻገር ለሚገኙ ካቶሊኮች እጅግ የተቀደሱ ቦታዎች የሚገኝባት ከተማ ስትሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ከተማዋ ‘ሎርድ ጂም’ (Lord Jim)፣ ‘ሃርት ኦፍ ዳርክነስ’ (Heart of Darkness) እና ‘ዘ ሻዶው ላይን’ (The Shadow Line) በመሳሰሉ ታላላቅ ልብ ወለዶች እና ታሪኮች የሚታወቀው የብሪታኒያዊ-ፖላንዳዊ ጸሐፊ ጆሴፍ ኮንራድ የትውልድ ስፍራ በመሆን ትታወቃለች።
ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከተማዋን ከጎበኙበት ጊዜ አንስቶ ሃያ አምስት ዓመታት አልፈዋል
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚህች ጥንታዊ ከተማ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት 25ኛ ዓመትን በማስመልከት በሚደረጉ ዝግጅቶች ማዕቀፍ ውስጥ በሚታይ እና ለዚህ ልዩ ዝግጅት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በሃገሪቱ የሚያደርጉት ጉብኝት በአራተኛው ቀን ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ይህ ጉብኝት የሁለትዮሽ ተልዕኮ ያለው፣ ማለትም ሃዋሪያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ያለው መሆኑን ገልጸው፥ ከፖለቲካ ባለስልጣናት ጋር የሚደረጉ በርካታ ስብሰባዎችንም ያካተተ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
“ከሁሉም በላይ ግን፣ ይህ ጉብኝት ‘በጸሎት ከእናንተ ጋር፣ በተለይም ከታማሚዎች እና መከራ ከሚቀበሉ ወገኖች ጋር አንድ እንድሆን’ በተለይም ‘ለምትወደደው’ ዩክሬን የሰላም እና የፍትህ ስጦታን ከእመቤታችን አማላጅነት እንድጠይቅ ያስችለኛል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ‘የጌታ እናት እና የቀርሜሌዎስ እመቤታችን እዚህ በሚከበረው ተዓምራዊ ምስል ፊት ለፊት ሆነን፣ ለእግዚአብሔር የምስጋና ጸሎታችንን እንዲሁም ሰላሙን እንዲሰጠን የምናቀርበውን ልመና ይዘን ወደ እሷ እንዞራለን’ ሲሉ የበዓሉ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል።
በኪዬቭ የከባድ ቦምብ ጥቃት የተፈጸመበት ምሽት
ለአራት ዓመታት ተኩል ያህል በዘለቀ ጦርነት ለወደመችው ሀገር ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ኪዬቭ በቅዳሜ እና እሁድ መካከል ባለው ምሽት ብቻ ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ማስተናገዷን፣ ከሌሊቱ 7፡25 እስከ 8፡45 ባለው ጊዜ ውስጥ ከባድ የሚሳኤል ጥቃቶች በዋና ከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ መፈጸማቸው ተነግሯል።
እንደ ባለስልጣናቱ መረጃ በዚህ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት ከ10 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ጥቃት ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ የተፈጸመ እጅግ ከባድ ጥቃት መሆኑ እየተገለጸ የሚገኝ ሲሆን፥ ከብራያንስክ፣ ከኩርስክ እና ከሮስቶቭ ከተሞች ከተተኮሱት ወደ 42 የሚጠጉ የሩሲያ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች እና ከመቶ የሚበልጡ ድሮኖች መካከል የተወሰኑት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እና ልዑካን ቡድናቸው በሚያርፉበት የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተወካይ ጽህፈት ቤት አካባቢ ላይ ማረፋቸው እና ፍንዳታዎቹ የህንፃውን የመስታወት በሮች ማነቃነቃቸውን እንዲሁም ይህንን ዘገባ ያቀረበው ሰው ጨምሮ አብዛኞቹ ሰራተኞች ምሽቱን በተዘጋጀው መጠለያ ውስጥ እንዲያሳልፉ ማስገደዱ ተገልጿል።
በበርዲቺቭ ቤተ መቅደስ መድረስ እና ከእመቤታችን ምስል ጋር መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በኪየቭ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ጋር በመሆን እሁድ ጠዋት በዚቶሚር ክልል በሚገኘው የቀርሜሊዮስ ገዳም የደረሱ ሲሆን፥ ብሔራዊ ቤተ መቅደስ ተብሎ የተሰየመው ይህ ገዳም የተመሰረተው የኪየቭ ገዢ በነበሩት ጃኑሽ ሎይስኪ ጥያቄ መሰረት እ.አ.አ. በ 1634 ዓ.ም. መሆኑ እና በ 1642 ዓ.ም. ደግሞ መቀደሱ ተነግሯል።
የባለሥልጣናቱ ተወካዮች እና እውቅና ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ጓዶች ከመላ ሃገሪቱ ከተውጣጡ በርካታ ምዕመናን እና ከሌሎች ልዑካን ጋር በመሆን ሊቀ ጳጳስ ጋላገርን በደስታ ለመቀበል በስፍራው የተገኙ ሲሆን፥ መስዋዕተ ቅዳሴው በተለያዩ አበቦች እና መንፈሳዊ መዝሙሮች በመታጀብ በደማቅ ሥነ ስርዓት መካሄዱ፣ እንዲሁም በሚያስገርም ሁኔታ በላቲን ሥርዓት በሚመሩት የዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ አባላት እና በዩክሬን የግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ በሆኑት ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ መታጀቡ ተነግሯል።
በቦታው የተገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቅዱስ መስቀሉን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ምስል በማስቀደም አብዛኛው ሰዎች የዩክሬን እና የፖላንድ ባንዲራዎችን በማውለብለብ መንፈሳዊ ዑደት ማድረጋቸው ተነግሯል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅርበት
በኪይቭ የዚቶሚር ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ቪታሊይ ክሪቪትስኪ በበኩላቸው ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ መልዕክት “በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉትን ሰዎች በተለየ ሁኔታ በልባችን እንድንይዝ አሳስባለሁ” ያሉ ሲሆን፥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምስጋናቸውን ከመግለጻቸው በፊት፣ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት እና የድንግል ማርያምን አማላጅነት እጅግ እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በሦስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ውስጥ የሚታየውን የጋራ ጭብጥ ከመዳሰሳቸው በፊት፣ “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ሰላምታ” ያደረሱ ሲሆን፣ “የብፁዕነቸውን መንፈሳዊ ቅርበት” ለሁሉም ካረጋገጡ በኋላ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ በጣሊያንኛ፣ እንዲሁም የመካከለኛው ክፍል በዩክሬንኛ የተነበበውን መልእክት በማስተንተን “ከፈጣሪያችን እና ከአዳኛችን ከእግዚአብሔር የተሻለ” የሰላምን መንገድ የሚያውቅ፣ የሰው ልጅን ስቃይ የሚረዳ፣ እንዲሁም የሕይወትን ትርጉም ለእኛ በመመለስ የሚያጠነክረን እና የሚያድሰን ማንም እንደሌለ አሳስበው፥ እንዲሁም “ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት” በተሻለ ሁኔታ ከእኛ ጋር አብሮ የሚጓዝ እና በእግዚአብሔር ፊት “ለእኛ” የሚማልድ ማንም ሊኖር አይችልም ብለዋል።
የጸሎት ኃይል እና ሰላም እንደ እግዚአብሔር ስጦታ
በአንደኛው መጽሐፈ ነግስት ነቢዩ ኤልያስ ጸሎቱ ተሰምቶ ጥያቄው እስኪፈጸምለት ድረስ ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር ሰባት ጊዜ ማቅረብ እንደነበረበት ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ነቢዩ ኤሊያስ በቀርሜሊዮስ ተራራ ላይ ከእግዚያብሄር ጋር መገናኘቱን፥ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር “ለሕዝቡ እና ለምድራቸው ሕይወት ሰጪ ዝናብን” እንደሚልክ እርግጠኛ መሆኑን እና ጸሎቱ በጽናት የተሞላ መሆኑን አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም፣ “ነቢዩ ኤልያስ በሰዎች የሚደርስበትን ረጅም የስደት ጊዜ በጽናት አልፎ እንደነበር አስታውሰው፥ እስከ መጨረሻው ድረስ ጽናቱን እና እምነቱን እንደገና አሳይቷል” ያሉ ሲሆን፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት የኤልያስ ምሳሌ እጆቻችንን እንዳንሰበስብ እና ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ በችግሮች መካከል ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ ይልቁንም በጸሎት ሳንታክት እንድንቀጥል እና በእግዚአብሔር ላይ ያለንን ተስፋ ሕያው አድርገን እንድንይዝ ያበረታታናል” ብለዋል።
ምንም እንኳን እግዚያብሄር በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምንባብ ውስጥ ምላሽ የማይሰጥ መስሎ ቢታይም፥ ከኤልያስ ሰባተኛ ሙከራ በኋላ ምልክት መላኩን እና ነቢዩ ኤሊያስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሰማይ ተመልክቶ ‘ከባሕር ላይ የወጣች በጣም ትንሽ ደመና’ ማየቱን፣ ብሎም በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ምላሽ በብዛት፣ በዝናብ መልክ እንደሚመጣ መረዳቱን አስታውሰዋል።
‘ይህ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ “እውነተኛ እና የተትረፈረፉ ጸጋዎች ከእግዚአብሔር ብቻ ሊመጡ እንደሚችሉ እንድንገነዘብ ይረዳናል’ ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ እንዲሰፍን የምንፈልገው ሰላም ከሁሉም በላይ “የእግዚአብሔር ስጦታ” መሆኑን ያስረዱ ሲሆን፥ በመቀጠልም ህዝቡ መጽናናቱን ማቆም ወይም ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት አሳስበው፥ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ብቸኛው ነገር በጽድቅ ተግባራት የታጀበ እምነት፣ ለኃጢያታችን ንስሐ መግባት፣ እንዲሁም ትሕትና እና የታመነ ጸሎት ነው ብለዋል።
ቀጣዩ የወንጌል ክፍል ለእመቤታችን የተሰጠ መሆኑን ያስረዱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ነቢዩ ኤልያስ በንባብ ውስጥ ለሕዝቡ ሲጸልይ እንደታየ ሁሉ፣ ዛሬ የክርስቶስ እናት እራሷ ስለ እኛ እንደምትጸልይ እና የምንፈልገውን አደራ የምንሰጠው ለእሷ እንደሆነ ገልጸዋል።
የወጣቶች ስጦታዎች፡ "የር.ሊ.ጳ. ሊዮ ቅርበት ደስታን ያመጣልናል"
በምዕመናን ጸሎት ወቅት ክርስቲያኖች በልባቸው ውስጥ ጥላቻን ከማሳደር እንዲጠበቁ የተለያዩ ጸሎቶች የቀረቡ ሲሆን፥ በቅዳሴው መገባደጃ ላይ የወጣት ወንዶችና ሴቶች ቡድን ለሊቀ ጳጳስ ጋላገር አበባዎችን እና ከእንጨት የተሰራ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ምስል ማበርከታቸው ተነግሯል።
“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከዩክሬን እና ከህዝቦቿ ጋር መቀራረባቸው በጣም የሚያስደስት ነገር ነው” በማለት በደስታ ስሜት ተሞልተው የተናገሩት ወጣቶቹ፥ “እዚህ ከእርሶ ጋር ስንሆን ቤተክርስቲያን አንድ የተዋሃደ ማህበረሰብ እንደሆነች ይሰማናል” ብለዋል።
ይሄንን ተከትሎ የዩክሬን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ በኪየቭ-ሃሊች የዩክሬናዊያን ግሪክ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዋና ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ስቪያቶላቭ፣ የአካባቢው አስተዳደር ተወካዮች እና በዩክሬን የሚገኙ ቀርሜላውያን ኃላፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በመጨረሻም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ምስል ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፣ ብፁዓን ጳጳሳቱ እና አብረዋቸው ቅዳሴውን ያከበሩት ካህናት ለተጨማሪ ጥቂት ደቂቃዎች ለጸሎት በቆዩበት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ መመለሱ ተነግሯል።
ሃምሌ 20 የሚደረጉ ስብሰባዎች
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ወደ ኪየቭ ተመልሰው እዚያም ከ ‘አጠቃላይ የዩክሬን አብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ድርጅቶች ምክር ቤት’ ተወካዮች ጋር እንደሚገናኙ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እየሰሩ ከሚገኙት አንድሪ ሲቢሃን እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን ጨምሮ ከፖለቲካ መሪዎች ጋር ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ስብሰባዎች ለማድረግ ቀጠሮ እንደተያዘላቸው ተነግሯል።