ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን - የማህደር ምስል ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን - የማህደር ምስል  

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የዩክሬን ሰላም እውን ሳይሆን በመቀረበት በአሁኑ ወቅት ከኢራን ጋር ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቀረቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በአንድ የመጽሐፍ ማስመረቂያ ዝግጅት ጎን ለጎን ባደረጉት ንግግር፣ "ለሃገሪቱ እና ለዓለም ጥቅም" ሲባል ከኢራን ጋር እንዲሁም በጋዛ ጉዳይ ላይ ወደ ድርድር እና ውይይት መመለስ እንደሚገባ ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ቤተክርስቲያን ያለማቋረጥ የምታስተላልፈው የሰላም መልዕክት ያለው አስፈላጊነት፣ እንዲሁም በውይይት፣ በዲፕሎማሲ እና በእርቅ አማካኝነት መከፋፈልን በማሸነፍ ረገድ ያለውን ሚና አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ረቡዕ ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በቅድስት መንበር የጣሊያን ኤምባሲ መቀመጫ በሆነው ‘ፓላዞ ቦሮሜኦ’ በተካሄደው የአንቶኒዮ ፕሬዚዮሲ "የትንሳኤው ሰላም፡ ከዮሐንስ 23ኛ እስከ ሊዮ 14ኛ - ወደ 2033ቱ ኢዩቤልዩ" በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ ይፋ በተደረገበት እና ከዝግጅቱ ጎን ለጎን ለጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ "እንደ አለመታደል ሆኖ ግጭቱ እየተባባሰ እና የሰላም ተስፋው እየተሟጠጠ በመምጣቱ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እየሄድን ያለ ይመስለኛል" ማለታቸው ተነግሯል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን ጦርነት ላይ ስለተከሰቱት አዳዲስ ሁኔታዎችን ሲናገሩ በቅርቡ የጦርነት ቀጠናውን ጎብኝተው የተመለሱትን በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገርን ጠቅሰው ‘እሁድ ምሽት ላይ እስካሁን ከተፈጸሙ ጥቃቶች መካከል በጣም ከባዱ ጥቃት መፈጸሙን’ ገልጸዋል።

ከኢራን ጋር ወደ ድርድር መመለስ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የኢራንን ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት የመግባቢያ ስምምነቱ ከአሁን በኋላ ተግባራዊ እንደማይሆን ጠቅሰው፥ እንዲሁም እየተፈጠረ ባለው ሁኔታ ላይ ያላቸውን ስጋት የገለጹ ሲሆን፥ ‘ይህ ግጭት እንዴት እንደሚያበቃ እንደማያውቁ፣ ይሄንን ጉዳይ ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሚያውቁት፣ ምናልባትም ማንም ሊያውቀው እንደማይችል ያላቸውን ሃሳብ አጋርተው፥ ቀደም ሲል የተፈረመው ስምምነት ውጤታማ ይሆናል ተብሎ የነበረውን ተስፋ አስታውሰዋል።

ካርዲናሉ እነዚህ ሁኔታዎች ሰላምን አደጋ ላይ ስለሚጥሉ፥ ዘላቂ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲባል ድርድሩ እንደገና እንደሚጀመር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ይህ "ለሃገሪቱ እና ለዓለም ጥቅም" አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

"እንቅፋቶችን በማስወገድ የሰላም ድልድዮች መገንባት"
የጣሊያን ጦር በጋዛ ሰርጥ መለያ ግምብ እየገነባ ስለመሆኑ እየተሰራጩ ስለሚገኙት ዘገባዎች የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ‘ይህንን በአንድ አባባል ማጠቃለል እንደሚቻል ጠቅሰው’፥ “ግድግዳዎችን ከመገንባት የሰላም ድልድዮች መገንባት ይገባል” በማለት የቅድስት መንበርን አቋም በድጋሚ አብራርተው፣ ይህ መርህ ቫቲካን ለጉዳዩ ያላትን አመለካከት እንደሚያንጸባርቅም ጭምር ገልጸዋል።

"ግጭት መቼም ቢሆን ውጤታማ አይደለም"
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከዚህም በተጨማሪ አብደራሂም ፋኪር የተባለ ሰው በፖሊስ ተይዞ ወደ መሬት ከተጣለ በኋላ ህይወቱ ያለፈበትን ክስተት ተከትሎ በጣሊያኗ ቦሎኛ ከተማ ስለተከሰተው ግጭት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፥ ካርዲናሉ ለተከሰተው ነገር የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ "እውነቱ እንዲረጋገጥ ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ" ያሉ ሲሆን፥ አስፈላጊው ምርመራ "በተረጋጋ ሁኔታ እና ያለ ምንም ግጭት" መከናወን እንዳለበት እና "ግጭት መቼም ቢሆን ውጤታማ አያደርግም" ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ሰላምን በማስፈን ረገድ የቤተክርስቲያኗ ሚና
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም ውይይትን እና ሰላምን ለማስፈን ቤተክርስቲያኗ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ይህንንም የተናገሩት እ.አ.አ. በ 2021 ዓ.ም. በሱቃቸው ላይ ዘረፋ የፈጸሙትን ሁለት ዘራፊዎችን በመግደላቸው እና አንዱን በማቁሰላቸው ምክንያት ጥፋተኛ ስለተባሉት የጌጣጌጥ ነጋዴ ስለሆኑት የማሪዮ ሮጌሮ ጉዳይ በጣሊያን ህዝባዊ ክርክር ውስጥ ካስነሳው ጠንካራ የቃላት ልውውጥ አንፃር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ቤተክርስቲያን ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ቃላትን መናገሯን ትቀጥላለች" ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፣ "የዘሪው ምሳሌ"ን በማስታወስ እነዚህ ቃላት "ፍሬ እንደሚያፈሩ" ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን ይህንን መልዕክት ዘወትር ለማስተላለፍ እንደማትሰለች ጠቁመው፥ ‘ምንም ዓይነት ውጤት ቢያስገኝም፣ ለሰላማዊ እና ዘላቂ ለሆነ አብሮነት ወሳኝ በሆኑት በእነዚህ እሴቶች ላይ መጽናት ትክክል እንደሆነ አስረድተዋል።

ስለ ቤተክርስቲያን የሰላም ተልዕኮ የተሰጠ አስተያየት
ካርዲናል ፓሮሊን "የሰላም ትንሳኤ፡ ከዮሐንስ 23ኛ እስከ ሊዮ 14ኛ - ወደ 2033ቱ የኢዩቤሊዩ በዓል" የተሰኘው መጽሐፍ በተመረቀበት መድረክ ላይ ንግግር ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ በተከታታይ በመጡት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘመናት ሁሉ ቤተክርስቲያን ለሰላም ያላትን ዘላቂ ቁርጠኝነት አስመልክተው አስተያየታቸውን መስጠታቸው ተነግሯል።

ይህ የሰላም መልዕክት የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪዎችን የሚያገናኝ "የሩጫ ቅብብሎሽ" እንደሆነ የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ እያንዳንዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቃላትም ሆነ በተጨባጭ ተግባራት ለውይይት፣ ለእርቅ እና ለሰላም በሚደረጉ ጥረቶች ለዓለም አቀፍ ስምምነትና አንድነት ጥረት አዲስ ጡብ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ‘ፓሴም ኢን ቴሪስ’ ጀምሮ "ከእንግዲህ ጦርነት ይብቃ!" እስከሚለው የቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሃዋሪያዊ መልዕክት፣ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ "በክፍልፋይ የሚካሄድ የዓለም ጦርነት" በማለት ያወገዙትን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ "ጦርነት ለሰው ልጅ ፈጽሞ የማይገባ ነው" በማለት የሰጡትን ተቃውሞ በማስታወስ ቤተክርስቲያኗ እርሳቸው "የሰላም ትንሳኤ" ብለው የጠሩትን ሰላም ማበረታታቷን መቀጠል አለባት ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአዲሱን መጽሐፍ የክርስቲያናዊ አንድነት ገጽታ አጉልተው በማሳየት፣ ወደ 2033ቱ ታላቁ ኢዮቤልዩ የሚደረገው ጉዞ የበለጠ ክርስቲያናዊ አንድነትን ሊያጎለብት እና መለያየትን በውይይት፣ በዲፕሎማሲ እና በእርቅ ለማሸነፍ የሚደረገውን ጥረት ሊያጠናክር እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ አጠቃለዋል።

24 Jul 2026, 14:45