ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በዩክሬን-ሊቪቭ ከሐይማኖት መሪዎች እና ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በዩክሬን-ሊቪቭ ከሐይማኖት መሪዎች እና ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር 

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በዩክሬን ለፍትሃዊ ሰላም ቅድመ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ጠየቁ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር እስከ ሐምሌ 14/2018 ዓ. ም. ድረስ ዩክሬንን እንደሚጎበኙ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ልኡክ ሆነው ወደ ዩክሬን የተጉዙት ብጹዕነታቸው በዩክሬን የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች የታደሱበት 35ኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በ “X” ገጹ፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በዩክሬን ጉብኝት የጀመሩት፥ በአገሪቱ የምትገኝ የላቲን ሥርዓት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች እድሳት 35ኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር እንደሆነ እና በዓሉ የሚከበረው በበርዲቺቭ በሚገኘው የቀርሜሎስ እመቤታችን ቤት መቅደስ ውስጥ እሁድ ሐምሌ 12/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ገልጿል። አጋጣሚው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2001 ዓ. ም. ወደ ዩክሬን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞን የሚያስታውስ መሆኑን አክሏል።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር የዩክሬን የአየር ክልል በመዘጋቱ ሐምሌ 9/2018 ዓ. ም. ወደ ፖላንድ ከተጓዙ በኋላ በኪየቭ የቅድስት መንበር እንደራሴ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ጋር በመኪና ወደ ዩክሬን እንደሚጓዙ እና እስከ ሐምሌ 14/2018 ዓ. ም. ድረስ በአገሪቱ ውስጥ እንደሚቆዩ ታውቋል።

የክራኮቬትስ ማቋረጭ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በፖላንድ የክራኮቬትስ ድንበር ሲያቋርጡ በዩክሬን የቅድስት መንበር አምባሳደር አንድሪ ዩራሽ እና በዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከዚያም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1998 ዓ. ም. በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ወደተካተተች ታሪካዊ ከተማ ሊቪቭ የተጓዙ ሲሆን፥ ሊቪቭ ከተለያዩ የታሪክ ዘመናት ጀምሮ የሥነ-ሕንፃ እና የባህል ተጽዕኖዎች ያላት እና በቅርብ ጊዜ በመጋቢት ወር መጨረሻ በሩሲያ በተሰነዘሩት ጥቃቶች የተጎዳች ከተማ መሆኗ ይታወሳል።

“በዚህ የአውሮፓ ክፍል ላይ ሰላምን መመለስ”

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር ዓርብ ሐምሌ 10/2018 ዓ. ም. ጠዋት ወደ ሊቪቭ ሲደርሱ የላቲን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚኤቺስላው ሞክሪዚኪ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር ቀጥሎም በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የክልል እና የማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናትን አነጋግረዋል።

“ጦርነቱን በትክክል ማቆም ማለት በዚህ የአውሮፓ ክፍል ሰላምን መልሶ ማቋቋም ማለት ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዩክሬንን ህዝብ ስቃይ እና መስዋዕትነታቸውን እንዳልረሱ ገልጸው፥ “ለፍትሃዊ ሰላም ትክክለኛ ሁኔታን መፍጠር አለብን” ብለዋል።

በዩክሬን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲን ያደረጉት ጉብኝት

ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር ቀጥለውም በካምፓሱም ሆነ በመስመር ላይ የተመዘገቡ፥ በግምት ወደ 30,000 የሚጠጉ ተማሪዎች ያሉበትን የዩክሬን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1998 ዓ. ም. ከመንግሥት በተገኘው መሬት ላይ የተመሠረተው ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያው ባሉ መንደሮች ላይ ጥቃቶች በሚፈጸሙባቸው ወቅት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ሰባት ፋኩልቲዎች እና መጠለያዎች ያሉት ሲሆን፥ ግቢው በቀጥታ ባይመታም በአቅራቢያው ባሉ መደሮች ላይ በተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች መጎዳቱ ይታወሳል።

ከሁለት ዓመት በፊት ሚሳኤል ከጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ወርዶ በርካታ ሰዎችን የገደለ ሲሆን፥ ተማሪዎችን እና ዘመዶችን ጨምሮ አርባ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸውን እንዳጡ ተነግሯል።

“ጦርነቱ እዚህ ላይ ደርሷል” ሲሉ የገለጹት የዩክሬን ግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቡነ ቦሪስ ጉድዚያክ ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገርን አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ የተቋሙን አካዳሚያዊ እና ማኅበራዊ ተነሳሽነቶችን በማስመልከት ንግግር አድርገዋል።

ከእነዚህም የቫቲካን ልዑካን አባላት ከተሳታፊዎች ጋር ተገናኝተው የዩኒቨርሲቲውን ኮሌጅ ምሥረታ ፕሮግራም ተከታታይ የእህት ማርያ ራዲስት ልምድ ያዳመጡ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ጉድዚያክ በንግግራቸው “ሁሉም ሰው ዕርዳታና ድጋፍ በመስጠት ላይ ተሰማርቷል” ብለው፥ “ተማሪዎችም ለሌሎች የሚስጥ አገልግሎትን የሚያካትት የተቀናጀ ትምህርት ያገኛሉ” ብለዋል።

ከሜጀር ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሼቭቹክ ጋር የተደረገ ግንኙነት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር ማምሻው ላይ በሪቭኔ የሚገኘውን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቤተ ክርስቲያን ከጎበኙ በኋላ በኪየቭ ወደሚገኘው ሐዋርያዊ እንደራሴ ተጉዘው እዚያም በኪየቭ-ሃሊች የዩክሬን-ግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

18 Jul 2026, 14:48