የተፈጥሮ ጸጋ፤ የተፈጥሮ ጸጋ፤  (AFP or licensors)

ቫቲካን የዓለም የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን ጭብጥ ይፋ አደረገች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በነሐሴ 26/2018 ዓ. ም. ለሚከበረው የዓለም የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን የመረጡት ርዕሥ ይፋ ሆኗል። ቅዱስነታቸው የመረጡት ርዕሥ፥ “...ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ...” (ኢሳ. 2:4) የሚል እንደሆነ ታውቋል። የቅዱስነታቸው መሪ ጭብጥ ይፋ የሆነው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በኩል እንደ ሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በየዓመቱ ለሚከበረው የዓለም የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን መሪ ጭብጥ ይሆን ዘንድ፥ በትንቢተ ኢሳ. 2:4 ላይ፥ “...ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ...” የሚለውን ጥቅስ መርጠዋል።

ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው፥ የቅዱስነታቸው መልዕክት በጦርነት እና በአካባቢ መራቆት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጎላ መሆኑን አስታውቋል።

እንዲህ ዓይነቱ የአካባቢ መራቆት ፍጥረትን የመንከባከብ ግዴታችን መጣሱን እና እንዲሁም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ለረጅም ጊዜ አደጋ መጋለጡን የሚያሳይ እንደሆነ ማግለጫው አስታውቋል።

ከዚህም በላይ “በአሁኑ ወቅት ጦርነት በተፈጥሮ ላይ ያለውን ተጽእኖ በስፋት አለመገንዘባችን በቂ ተቋማት እንዲፈጠሩ ወይም ግጭቶችን ለመከላከል እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የታለሙ ኃላፊነት የሚሰማቸው ውሳኔዎች እንዲሰጡ አላደረገም” ሲል አክሏል።

መግለጫው በመጨረሻም፥ ነቢዩ ኢሳይያስ የጦር መሣሪያዎች ወደ ግብርና መሣሪያዎች መለወጥ እንዳለባቸው የሚተነብይበት ክፍል፥ “ከዓመፅ እና ከውድመት ይልቅ ለልማት እና ዘላቂነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የቀረበ ግልጽ ግብዣ ነው” ሲል ደምድሟል።

 

03 Jun 2026, 09:46