ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከመደበኛው የካርዲናሎች ጉባኤ ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከመደበኛው የካርዲናሎች ጉባኤ ጋር   (@VATICAN MEDIA)

ቫቲካን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጠሩት የካርዲናሎች ስብሰባ የጊዜ ሰሌዳን ይፋ አደረገ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከካርዲናሎች ጉባኤ አባላት ጋር ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ እና ዓለም ወቅታዊ ሁኔታ፣ ከሰላም ፍለጋ እና ከሲኖዶሱ እቅዶስ ትግበራ ጋር በተያያዘ ትኩረት በሚሰጥባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የሚወያይ ልዩ ስብሰባን ከሰኔ 19-20/2018 ዓ. ም. እንደሚያካሂዱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ከሰኔ 19-20 የሚካሄደውን ልዩ የካርዲናሎች ስብሰባ መርሃ ግብር ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ይህም ከቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ቀደም ብሎ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከካርዲናሎች ጋር በሚገናኙበት ወቅት ዓለምን ስለሚያስጨንቁ ግጭቶች እና ቤተ ክርስቲያኗ ሰላምን እና እርቅን ለመገንባት በቋንቋ እና በአመለካከት መግባባት ባለችባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ታውቋል።

ስብሰባው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከዚህ በፊት በጥር ወር ላይ ከዓለም ዙሪያ ከመጡ መራጭ እና መራጭ ካልሆኑ 170 ካርዲናሎች ጋር ያደረጉትን ስብሰባን ተከትሎ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በስብሰባው መዝጊያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከእናንተ ጋር በሰኔ ወር በሚካሄድ ስብሰባ መተማመን እንዳለብኝ ይሰማኛል” ሲሉ ለካርዲናሎቹ መናገራቸው ይታወሳል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት ውይይቱ በጸሎት፣ በግል የጽሞና አስተንትኖ፣ በቡድን ውይይት እና በጠቅላላ ስብሰባ በሲኖዶሳዊነት መንገድ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ካርዲናሎቹ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሹ ውስጥ የሚደረገው ውይይት ሚስጥራዊነት እንዲጠብቁ እና የወንድማማችነት ድባብን ለመጠበቅ ሲባል በስብሰባው ወቅት መግለጫ እንዳይሰጡ ተጠይቀዋል።

አራት የአስተንትኖ ጊዜያት

የስብሰባው ተካፋዮች በ20 ቡድኖች የተከፈሉ ሲሆን፥ ዘጠኝ ቡድኖች መራጭ የሆኑ መደበኛ ካርዲናሎችን ያቀፈ፥ ከእነዚህም ውስጥ ሐዋርያዊ እንደራሴዎችን እና መደበኛ ሆነው ነገር ግን አገልግሎታቸውን የጨረሱ ካርዲናሎችን እንደሚያካትቱ ታውቋል።

ሌሎች አሥራ አንድ ቡድኖች በሮማ ኩሪያ ሥር የሚገኙ መራጭ እና መራጭ ያልሆኑ ካርዲናሎኖችን እንደሚያካትቱ ታውቋል።

እያንዳንዱ ቡድን ውይይቱን የሚመራ እና ጊዜውን የቆጣጠር ፕሬዝዳንት እና አስተያየቶችን የሚሰበስብ እና የቡድኑን የመጨረሻ ሪፖርት የሚያዘጋጅ ጸሐፊ እንደሚኖረው ታውቋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሚመራው ይህ የካርዲናሎች ስብሰባ ዓርብ ሰኔ 19/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚጀምር ታውቋል።

ካርዲናሎቹ ቀጥለውም ለመክፈቻው ሥነ-ሥርዓቱ ወደ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ የሚሄዱ ሲሆን፥ በዚህ ዝግጅት ላይ የካርዲናሎች ጉባኤ ተጠሪ የሆኑት ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ንግግር ካደረጉ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመግቢያ ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ “ወንጌልን በምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ለማወጅ ተጠርተናል?” በሚለው ጥያቄ የሚያተኩር ሲሆን፥ የክራኮቫው ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ግሪዝጎርዝ ራይሽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተንትኖን ካቀረቡ በኋላ የጽሞና ጸሎት ቀርቦ የቡድን ውይይት እና ሪፖርቶች በጠቅላላ የስብሰባ ክፍለ ጊዜ ላይ እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ዓርብ ከሰዓት በኋላ በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ “የኃይል ባሕል እና የፍቅር ስልጣኔ” በሚለው ጭብጥ ላይ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፌርናንደዝ “የስዎች አስደናቂነት” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ ምዕራፍ 5ን በመጥቀስ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ታውቋል።

የጋራ ጥቅምን መገንባት

ቅዳሜ ሰኔ 20/2018 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በካርዲናል ሬ የሚመራው መስዋዕተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ካርዲናሎቹ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

ሦስተኛው ክፍለ ጊዜ “የዘመናችን የሥራ ቦታዎችን በበጎ ነገር መገንባት” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ስብሰባ

የጆሃንስበርግ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ እና የደቡብ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ካርዲናል እስጢፋኖስ ብሪስሊን እንደሚመሩት ታውቋል።

ውይይቱ የጋራ ጥቅም ግንባታን አስቸጋሪ በሚያደርጉት ስብራቶች ላይ፣ ከሕዝቦች እና ከማኅበረሰቦች በሚነሱ ጥያቄዎች እና የአካባቢ አብያተ ክርስቲያናት እና ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን ሊሰጡ በሚችሉት ድጋፎች ላይ እንደሚያተኩር ታውቋል።

አራተኛው እና የመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በአዲሱ ሲኖዶስ አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን፥“ሲኖዶሱ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ” በሚለው ላይ ውይይት ይካሄዳል። የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2027-2028 ዓ. ም. ድረስ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባዎች፡ ደረጃዎች፣ መስፈርቶች እና የዝግጅት መሣሪያዎች ጀምሮ በሠነዱ ጭብጥ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

ክፍለ ጊዜው የማብራሪያ ጥያቄዎችን፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር የሚደረግ ውይይት እና እያንዳንዳቸው ከሦስት ደቂቃዎች የማይበልጡ ነፃ አስተያየቶችን ያካትታል።

ጠቅላላው የካርዲናሎች ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚያደርጉት የማጠቃለያ ንግግር የሚፈጸም ሲሆን፥ ቀጥሎም የምስጋና ጸሎት ከቀረበ በኋላ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ውስጥ የተዘጋጀውን  እራት ግብዣ ካርዲናሎቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ይካፈላሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሰኔ 22/2018 ዓ. ም. ዓመታዊ የቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ይመራሉ።

 

24 Jun 2026, 17:57