በቅድስት መንበር ተወካይ በሚመራው የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮንቮይ ላይ ተኩስ መከፈቱ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሊባኖስ የሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ፓኦሎ ቦርጃ ከካሪታስ እና ከሌሎች የካቶሊክ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሰኔ 4/2018 ዓ. ም. በሴዳር ደቡባዊ ክፍል ወደሚገኙ ሦስት የክርስቲያን መንደሮች ሲጓዙ የነበሩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተሽከርካሪዎች በእስራኤል ጦር እና በሂዝቦላህ መካከል በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት መንገዳቸውን እንዲቀይሩ መገደዳቸው ታውቋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦርጃ ለቫቲካን ሚዲያዎች እንደዘገቡት፥ ከቤሩት ጠዋት ተነስተው የነበሩት 45 የጭነት መኪናዎች እና ተሽከርካሪዎች ቡድን የጢሮስ ደቡባዊ ክፍል ወደሆነች ዴቤል ከመድረሳቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ተኩስ መከፈቱን አብራርተዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦርጃ፥ በተፈጠረው ተጨማሪ አለመረጋጋት ምክንያት “ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በተቀናጀው መንገድ መቀጠል አልተቻለም” ሲሉ አብራርተዋል፣
የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ ዕርዳታ አቅርቦት
“ሁላችንም የተለያዩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በተለይም የምግብ አቅርቦቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ ውሃን፣ መድሃኒቶችን እና ነዳጅን በጫነ ረጅም ኮንቮይ ውስጥ ነበርን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦርጃ፥ ይህ የዕርዳታ ቁሳቁስ ለዴቤል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሁለት መንደሮች አይን ኤቤል እና ራምኢችም ጭምር እንደሆነ አስረድተው፥ አሁኑ ባለው የአቅርቦት እጥረት ምክንያት በአካባቢው ለሚገኙ ሱቆች ለማከፋፈል የታሰቡ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁም በመንደሮች ውስጥ ሕይወት ቀስ በቀስ እንዲጀምር ለማድረግ ገበሬዎችን እና ከብት አርቢዎችን ለመርዳት የታሰበ እንደ ነበር ገልጸዋል።
ከተሽከርካሪዎቹ መካከል የአካባቢውን ነዋሪዎች የያዙ መኪኖችም እንደ ነበሩ የተነገረ ሲሆን፥ ለሳምንታት ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ቤታቸው መመለስ የሚፈልጉ እንደ ነበር ታውቋል። ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በተዋጊዎች መካከል ተኩሱ ሲፈጸም የነበረበት ቦታ በመሆኑ ምንም ዓይነት ድንጋጤ እንዳልነበረ ተናግረው፥ እነዚህ አስፈሪ ሁኔታዎች ቢሆኑም ነገር ግን ሰዎች ራሳቸውን በእርጋታ ለማቋቋም እና ለማረጋጋት እንደሚሞክሩ ሊቀ ጳጳሱ ተናግረዋል።
የቁሳቁስ ዕርዳታ እና በሥፍራው የቤተ ክርስቲያን መገኘት
የዕርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ መኪኖች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ለመጓዝ አዲስ ፈቃድ በማግኘት ሙሉ በሙሉ የተለየ መንገድ መውሰድ ነበረቻቸው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦርጃ፥ ከ10 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ወደ ዴቤል መድረሳቸውን ገልጸዋል።
እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ተለይተው ለሚገኙ መንደሮች ዕርዳታን ማድረስ ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ቦርጃ፥ ዋና ግቡ የተፈናቀሉትን ወደ አካባቢዎቻቸው መመለስ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ በጦርነት ውስጥ ቢንሆኑም ሕዝቡን ለመርዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚቀጥሉ እና በቀጣዩ ሳምንት ሌላ ኮንቮይ እንደሚኖር ተናግረዋል።
የትላንትናው ተልዕኮ በሊባኖስ ውስጥ ጦርነት ከተጀመረበት ከየካቲት 23/2018 ዓ. ም. ወዲህ የተላኩ 17 የሰብዓዊ ዕርዳታ ተሽከርካሪዎች እና 3 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ጨምሮ ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ የተደረጉ 20ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች እንደ ነበሩ ታውቋል።
“ሊባኖስ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መኖር አስፈላጊ ነው” ሲሉ የቀጠሉት ሊቀ ጳጳስ ቦርጃ፥ “ይህም ሰዎች በማህበረሰባቸው ውስጥ የመቆየት እና የመትረፍ ዕድል እንደሚሰጣቸው እና ከቁሳዊ ድጋፍም በላይ ነው” ብለው፥ የእኛ በሥፍራው መገኘት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን እና የሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን መገኘትን አንድ ያደርጋል” ብለው፥ “ምክንያቱም ሰዎች የቤተ ክርስቲያኗን ፍቅር እና አብራቸው እንደሆነች ሊሰማቸው ይገባል” ብለዋል።