የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የገዳማውያት ኅብረት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የገዳማውያት ኅብረት  

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ገዳማውያት በአንድነት እና በተስፋ እንደሚጓዙ ተገለጸ

ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ከ130 በላይ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ገዳማውያት በታንዛኒያ መዲና ዳሬሰላም ተገናኝተው፥ ማኅበረሰቦቻቸውን ለማጠናከር እና የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ የሚያግዙ ተሞክሮዎችን፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና ስኬቶችን እንዲሁም ዘዴዎችን ማስተማር የሚችሉ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ኮንራድ ኤን. ሂልተን” በተሰኘ ፋውንዴሽን የሚመራው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን፣ የልማት አጋሮችን፣ የፋውንዴሽኑ ደጋፊዎችን፣ ሌሎች ተባባሪዎችን እና እንዲሁም ከ23 አገራት የተወጣጡ ገዳማውያትን ያሳተፈ ስብሰባ በታንዛኒያ መዲና ዳሬሰላም ከሰኔ 3-5/2018 ዓ. ም. የተካሄደ ሲሆን፥ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ንግግር ያደረጉት የፕሮግራም ኦፕሬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኮንራድ ኤን. ሂልተን ፋውንዴሽን የገዳማውያት ኅብረት መሪ እህት ጄን ዋካሂዩ እንደሆኑ ታውቋል።

ማኅበረሰቦችን በትብብር ማጠናከር

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2026 ዓ. ም. የተካሄደው የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት ጉባኤ መሪ ጭብጥ፥ “በአንድነት እና በተስፋ አብረን በመጓዝ ማኅበረሰቦችን ማጠናከር እና የጋራ ጥቅምን በጋራ ማሳመር” የሚል ሲሆን፥ ስብሰባው ተሳታፊዎቹ በአካባቢ፣ በክልል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአገልግሎታቸው የተገኙ ልምዶችን ለመጋራት ዕድል ሰጥቷቸዋል።

ውይይቶቹ በአንድነት፣ በሰብዓዊ ክብር፣ በማኅበረሰብ ለውጥ፣ በታሪክ አጻጻፍ፣ በጋራ ጥቅም እና ለዘመናዊ ተግዳሮቶች በጋራ ምላሾች በመስጠት ላይ ያተኮሩ እንደ ነበሩ ተመልክቷል።

ማዕከላዊ ጠባቂ ክርስቶስ ነው

በስብሰባው ላይ ንግግር ካደረጉት መካከል አንዱ በሮም የግሪጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ሰው ጥናት፣ ሰብዓዊ ክብር እና እንክብካቤ ኢንስቲትዩት (IADC) ዳይሬክተር የሆኑት አባ ሃንስ ዞልነር ሲሆኑ፥ በንግግራቸውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረጉ ጥረቶች በወንጌል ላይ መመሥረት እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ማዕከላዊ ጠባቂው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ያሉት አባ ሃንስ ዞልነር፥ “ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ማለት አሰቃቂ በደል እና ስቃይ ያጋጠማቸውን ሰዎች መንከባከብ እና መርዳት ማለት ነው” ሲሉ አስረድተው፥ የኮንራድ ኤን. ሂልተን ፋውንዴሽን በዓለም ዙሪያ ገዳማውያትን ለማሰልጥን እና ለማብቃት የሚያደርገውን ዘላቂ ድጋፍ አድንቀዋል።

ገዳማውያቱ ፋውንዴሽኑ በሚያደርገው ድጋፍ አማካኝነት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን ማዳን፣ ለወጣቶች የሚሰጥ ትምህርት ማስፋፋት፣ ለሴቶች የሙያ ስልጠናን መስጠት፣ የአካባቢውን ማኅበረሰቦች ማጠናከር እና ከፍተኛ የትምህርት ዕድልሎች ማመቻቸት መቻላቸው አባ ሃንስ ገልጸዋል።

እንዲሁም የኔትወርክ እና የትብብር አገልግሎት አስፈላጊነትን በማጉላት፥ በልዩ ልዩ የገዳማውያት ማኅበራት እና ድርጅቶች መካከል ያለው አጋርነት ለማኅበራዊ ፍላጎቶች ምላሽ በመስጠት ውጤታማነትን እና ዘላቂነትን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።

የፕሮግራም ኦፕሬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እህት ጄን ዋካሂዩ ለተሳታፊዎች ገለጻ ሲያደርጉ
የፕሮግራም ኦፕሬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እህት ጄን ዋካሂዩ ለተሳታፊዎች ገለጻ ሲያደርጉ

ማዳመጥ፣ መማር፣ አዳዲስ በሮችን መክፈት

የፕሮግራም ኦፕሬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኮንራድ ኤን. ሂልተን ፋውንዴሽን የገዳማውያት ኅብረት መሪ እህት ጄን ዋካሂዩ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ በስብሰባው ወቅት ገዳማውያቱ የማዳመጥ እና የግልጽነት መንፈስ እንዲኖራቸው አበረታትተው፥ በፋውንዴሽኑ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ራዕይ ያለው አመራርን የሚያካትት የካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት ዋና እሴቶች ርህራሄ፣ ትህትና፣ ታማኝነት እንደሆኑ የገለጹት እህት ጄን ዋካሂዩ፥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና በጾታ ላይ የተመሠረተ ጥቃትን በመከላከል ጥበቃን ማድረግ፣ ወጣቶችን ማብቃት እና ለአረጋውያን ገዳማውያት እንክብካቤ ቅድሚያን መስጠት እንደሆነ ተናግረው፥ ጥበቃን የማድረግ ባህል ማሳደግ፥ ግለሰቦችን ከጥቃት፣ ከብዝበዛ፣ ከዓመፅ እና ከጉዳት የሚከላከሉ እርምጃዎችን መተግበር እንደሚጨምር አፅንዖት ሰጥተዋል።

በመተባበር አብሮ መጓዝ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፎርቱናተስ ንዋቹኩዌ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፥ በዕለት ተዕለት የኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ የሰውን ክብር መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ የጥቃት ሰለባዎችን እና ተጎጂዎችን ማዳመጥ በፈውስ ሂደት ውስጥ ተጠያቂነት እንዲኖር እና ፍትህን ለማምጣት አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።

ከቫቲካን ከመጡት የስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል በቅድስት መንበር  የሰብዓዊ ልማት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ጸሐፊ አቡነ ሉዊስ ማኑዌል አሊ ሄሬራ፣ የገዳም ሕይወት ተቋማት እና የሐዋርያት ሕይወት ማኅበራት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አባ ኤይተር ጂሜኔዝ፣ በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤተ ሥነ-መለኮታዊ የሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ናታሻ ጎቬካርን እና ሌሎች ሃላፊዎችም እንደሚገኙበት ታውቋል።

ተባባሪ ቤተ ክርስቲያን መገንባት

የምሥራቅ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ዋና ጸሐፊ አባ አንቶኒ ማኩንዴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ ኅብረቱ በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ከሚገኙ የገዳማውያት ማኅበራት (ACWECA) ጋር በመተባበር፥ በምሥራቅ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ውስጥ በብጹዓን ጳጳሳት፣ በካኅናት፣ በገዳማውያን እና ገዳማውያት መካከል የሚደረገውን ውይይት ማበረታታት መቀጠሉን ገልጸው፥ እንዲህ ዓይነት ትብብር በክልላዊ፣ በአገር አቀፍ እና በአህጉረ ስብከት ደረጃ ሲኖዶሳዊ መዋቅሮችን እና ትስስር እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።

የገዳማውያት ተነሳሽነት ስብሰባ በየሦስት ዓመቱ በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህም በገዳማውያቱ እና በአጋሮቻቸው መካከል ግንኙነትን በማሳደግ ለጋራ ትምህርት ጠቃሚ መድረክ እንደሚያዘጋጅ ታውቋል።

የኅብረት እና የተስፋ ምስክር

የመክፈቻውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት የዳሬሰላም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ይሁዳ ታዴዎስ ሩዋኢቺ ገዳማውያቱ በመንፈሳዊ ትውፊታቸው እና በሐዋርያዊ ተነሳሽነታቸው ጸንተው እንዲቀጥሉ አሳስበው፥ በጉባኤው ወቅት የተከበረውን የቅዱስ በርናባስ ዓመታዊ በዓል አስታውሰው፥ ቅዱሱን የትሕትና አገልግሎት አብነት በማድረግ፥ “እንደ ቅዱስ በርናባስ ገዳማውያቱ ዛሬም በጥምቀት እና በታማኝነት ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል ተጠርተዋል” ብለዋል።

በታንዛኒያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንጄሎ አካቲኖ በመዝጊያው የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በገዳም ሕይወት ውስጥ ራስን በመስዋዕትነት የመስጠት አስፈላጊነት ገልጸው፥ ትብብር ገዳማውያቱ ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በብቃት እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቀጣይነት ያለው ትምህርት እና ሕንጸት ለሚስዮናዊ ደቀ መዝሙርነት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው፥ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በምንፈልግበት ወቅት እንደ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኅብረት ስንጓዝ ትምህርት የተልዕኳችን እምብርት ሆኖ መቆየት አለበት” ብለዋል።

ጉባኤው በተሳታፊዎች መካከል አብሮነትን ለማጎልበት፣ የጥበቃ ተግባራትን ለማጠናከር እና ለጋራ ጥቅም ትብብርን ለማጠናከር በተወሰደው አዲስ ቁርጠኝነት ተጠናቋል።

15 Jun 2026, 16:39