ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ “መርከብ ፈጽሞ የመገለል ቦታ መሆን የለበትም ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዓለም ዙሪያ ያሉ አብያት ክርስቲያናት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየዓመቱ በሐምሌ ወር ሁለተኛ እሁድ የባሕር ቀን እሑድን በማክበር የባሕር ላይ ሠራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ይታወቃል። ዘንድሮ በዓሉ እሑድ ሐምሌ 5/2018 ዓ. ም. የሚከበር ሲሆን፥ መሪ ጭብጡም “ቤተ ክርስቲያን ከባሕር ላይ ሠራተኞች ጎን የምትሆንባቸው የተስፋ ወደቦች” የሚል እንደሆነ ተገልጿል።
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ለባሕር ቀን መታሰቢያ እሁድ በጻፉት መልዕክት፥ ባሕር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የንግድ ዕቃ ከሚጓጓዝበት ባሻገር በርካታ ሰዎች የሚገኙበት ሥፍራ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር ላይ ሰዎች ከሥራቸው በላይ ናቸው
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በመልዕክታቸው፥ ዓለም በባሕር፣ በሐይቆች፣ በወንዞች እና በውሃ መንገዶች ላይ መመካት መቀጠሉን ገልጸው፥ ይሁን እንጂ ከባሕር ዳርቻ ንግድ ጀርባ ሥራቸው ከውሃ መስመሮች ጋር የተሳሰረ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በርካታ ማኅበረሰቦች እና ቤተሰቦች የኑሮ መተዳደሪያ እና መተማመኛቸው እነዚህ ወንዶች እና ሴቶች እንደሆኑ ገልጸው፥ “የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ቀውስ የሰው ልጅ በባሕር እና በላይ በሚሠሩት ላይ ምን ያህል እንደሚመካ ዓለም ያስታውሳል” ሲሉ ካርዲናል ቼርኒ አብራርተዋል።
ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በባሕር መታሰቢያ ቀን እሑድ እነዚህን ወንዶች እና ሴቶች የምታስታውሳቸው በሚሠሩት ሥራ ወይም በሚያጓጉዟቸው ዕቃዎች ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠሩ፣ የማይደፈር ክብር ያላቸው የሰው ልጆች መሆናቸውን በማመን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
እያንዳንዱ የወደብ ወይም የባሕር ላይ ሠራተኛ ታሪክ እንዳለው የገለጹት ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ “የባሕር ላይ ሠራተኛ ሊታይ እና ሊከበር ይገባዋል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የመገለል ስሜት
በባሕር ላይ ሠራተኞች ልብ ውስጥ አሁንም እርግጠኛ አለመሆን እንዳለ የጠቆሙት ካርዲናል ቼርኒ፥ “ለረጅም ዓመታ ሕዝቦችን እና አገራትን ሲያገናኝ በቆየው ባሕር ላይ ውጥረት፣ አለመረጋጋት፣ ጦርነት እና ፍርሃት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው፥ የቡድኑ አባላት ውሃው ላይ የሚያጋጥማቸውን አደጋ መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን የግጭት መዘዝ፣ የምግብ እጥረት፣ መታሰር እና ፍርሃት እንደሚያጋጥማቸዋል አስረድተው፥ “ይህም ከኅብረተሰቡ የመገለል፣ ከቤተሰብ የመለየት እና የድካም ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል” ብለዋል።
“ቴክኖሎጂም ቢሆን ብዙዎችን የበለጠ ብቸኞች አድርጓቸዋል” ያሉት ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ የሰውን ልጅ መቀራረብ እየከበደው መምጣቱን ተናግረው፥ “የባሕር ላይ ሠራተኞች ቁጥራቸው እየቀነሰ፣ በባሕር ዳርቻ የሚሆኑበት ጊዜ እያጠረ፣ የሥራ ጫና እና የተጣበበ የጊዜ ሰሌዳ እየጨመረ መምጣቱን ያያሉ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰዎች አስደናቂነት” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው እንዳስጠነቀቁት፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ሰዎችን ወደ መረጃነት፣ ወደ መሣሪያነት ወይም ወደ ሸቀጥነት ሳይቀንሱ ነገር ግን በምትኩ፣ ሰብዓዊ ክብርን እና ነፃነትን መጠበቅ አለባቸው” ብለው፥ በመሆኑም መርከብ የመገለል ወይም የግዴለሽነት ቦታ ከመሆን ይልቅ ሰዎች ተራርቀው ቢኖሩም ጎን ለጎን አብረው የሚኖሩበት ቦታ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ባሕር አንድ ያደርገናል
ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ ባሕር ሰዎች በወንድማማችነት፣ በአንድነት እና በአክብሮት የሚኖሩበት ልዩ ልዩ ዜግነት፣ ባሕሎች እና እምነቶች ያሏቸው ሰዎች ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፥ ባሕር አንዳችን ለሌላው መኖራችንን የሚያስተምረን፣ ውቅያኖሶች ሰዎችን የሚከፋፍሉ ሳይሆን የሚያገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዱ የባሕር ላይ ሠራተኛ ብቻውን ወይም የተረሳ አለመሆኑን ለማስታወስ እየሠራች መሆኗን ተናግረዋል።
ከዚህም በላይ ውቅያኖስ የንግድ እና የጉዞ መስመሮች ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ እንዲንከባከብ የተሰጠ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንደሆነ ገልጸው፥ ሆኖም የዓለም የውሃ መስመሮች በብክለት፣ በአካባቢ መበላሸት እና በብዝበዛ እንደሚሰቃይ እና ወደ 88% የሚሆነው የባሕር ወለል በፕላስቲክ መበከሉን እንዲሁም እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2018 ዓ. ም. ከዓለም 90% የሚሆነው የዓሣ አቅርቦት ተበክሎ ወይም ተሟጦ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
ይህም የባሕር ላይ ሕይወት ወይም ሠራተኞች ችግር ብቻ እንዳልሆነ የተናገሩት ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ “ውቅያኖሶች ሲሰቃዩ የሰው ልጅም አብሮአቸው ይሰቃያል” ሲሉ አስጠንቅቀው፥ የባሕር ሕይወትን መጠበቅ፣ ሥነ-ምግባራዊ እና ዘላቂ ልምዶችን ማስተዋወቅ፣ የባሕር ላይ ሠራተኞችን ክብር እና ደኅንነት መጠበቅ እና መንከባከብ ዓለም አቀፍ ኃላፊነትን ማዳበር የሁሉም ኃላፊነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ኃላፊነት ልትርቅ አትችልም” ያሉት ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ ይልቁንም ለባሕር ላይ ሠራተኞች ቅርብ በመሆን ወደ መርከቡ ውስጥ እንድትገባ፣ አብረዋቸው እንድጓዝ፣ እንድታዳምጣቸው፣ እንድታጽናናቸው፣ ሰብዓዊ ክብርን እንድታስጠብቅ እና በሰው ልጅ ሕይወት መካከል ግልጽ የተስፋ ምልክት እና መኖሪያ እንድትሆን ተጠርታለች” ብለዋል።
የባሕር ላይ ተጓዦችን እንዲያገለግሉ በተመደቡ ካኅናት አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ረጅሙን የባሕር ላይ ሐዋርያነት መቀጠል እንደምትችል እና “አገልግሎቱም ለእያንዳንዱ ተሳፋሪ፣ ዓሣ አጥማጅ፣ የባሕር ላይ እና የመርከብ ውስጥ ሠራተኛ ሕይወት ዋጋን በመስጠት ብቻውን አለመሆኑን ለማሳሰብ ነው” ሲሉ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በመልዕክታቸው አስረድተዋል።