ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለጋዜጠኞች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለጋዜጠኞች ምላሽ በሰጡበት ወቅት  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስለ ሰላም እየሰበኩ ወደፊት የሚጓዙ መሆናቸው ተነገረ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በጣሊያን ሳን ጆቫኒ ሮቶንዶ በሚገኘው የ “ካዛ ሶሊዬቮ ዴላ ሶፈሬንዛ” ሆስፒታል 70ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ከተገኙት ጋር ጎን ለጎን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ትራምፕ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የተናገሩትን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ብጹዕነታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቀድሞውኑ ምላሽ የሰጡበት መሆኑን አስታውሰው፥ “የቅዱስነታቸው ምላሽ ሚናቸውን በሚገባ የሚገልጽ ክርስቲያናዊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወንጌልን መሠረት በማድረግ ስለ ሰላም እየሰበኩ ወደፊት መጓዝ ይቀጥላሉ” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱ፥ ‘ጊዜው ቢመችም ባይመችም ቃሉን ስበክ’ ባለው መሠረት ቅዱስነታቸው ወንጌልን እየሰበኩ፣ ስለ ሰላምም እየሰበኩ ወደ ፊት ይጓዛሉ” ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህንን የተናገሩት በሳን ጆቫኒ ሮቶንዶ በሚገኘው የ “ካዛ ሶሊዬቮ ዴላ ሶፈሬንዛ” ሆስፒታል 70ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ሲሆን፥ ሆስፒታሉ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1956 ዓ. ም. ወደ ሳን ጆቫኒ ሮቶንዶ በመጣው ታዋቂው የካፑቺን ፍራንችስካዊ ካኅን ቅዱስ አባ ፒዮ የተመሠረተ እንደ ነበር ይታወሳል። በደቡባዊ ጣሊያን ካሉት ትላልቅ የሕክምና ማዕከላት መካከል አንዱ ሲሆን፥ ለሕሙማን እንክብካቤን በመስጠት፣ በምርምር እና በሕክምና ማዕከሎቹ ይታወቃል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ማርኮ ሩቢዮ ወደ ቫቲካን ከመምጣታቸው ከሦስት ቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14 ላይ የፈጸሙትን ሌላ ጥቃት በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

“ወደ ፊት አዳዲስ ጥቃቶች ቢከሰቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምላሽ የመስጠት ዕድል ይኖራቸው እንደሆነ አላውቅም” ሲሉ ካርዲናሉ ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቀደም ሲል ለጋዜጠኞች የሰጧቸው አስተያየቶች በአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በጉዞ ላይ እያሉ እንደ ነበር አስታውሰው፥ መልዕክታቸው አሁንም ተመሳሳይ እንደ ሆነ በድጋሚ ገልጸዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስቀድመው ምላሽ የሰጡበት በመሆኑ ምንም አልጨምርም” ሲሉ ብጹዕነታቸው ተናግረው፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ምላሽ እጅግ በጣም ክርስቲያናዊ ነው፤ ሚናቸው የሚፈልገውን እያደረጉ ነው፤ አስደሳች ይሁን አይሁን ያ ሌላ ጉዳይ ሆኖ ነገር ግን ዋና ተልዕኮአቸው ሰላምን መስበክ ነው፤” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አቋም እንደሌለው እንረዳለን። ነገር ግን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ምላሽ ይህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

 

07 May 2026, 13:21