በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት 

ቅድስት መንበር የኒውክሌር መከላከያ ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋትን እንደሚያባብስ አስጠነቀቀች

ቅድስት መንበር የጦር መሣሪያ ትጥቅ እንዲፈታ እና የብዙ አገራት የጋራ ተሳትፎ እንዲኖር ጥሪ በማድረግ፥ የኒውክሌር መከላከያ፣ የጦር መሣሪያ ዘመናዊነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚመሩ ወታደራዊ ሥርዓቶች አስከፊ የስሌት ስህተት አደጋን እየጨመሩ መሆናቸውን አስጠንቅቃለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር በኒውክሌር መከላከያ፣ የጦር መሣሪያ ዘመናዊነት እና በወታደራዊ ሥርዓቶች ውስጥ የአርቴፊሻል ኢንቴለጀንስ ውህደት መጨመር ዓለምን ከጊዜ ወደ ጊዜ አደገኛ በሆነ መንገድ ላይ እያስቀመጣት መሆኑን አስጠንቅቃለች።

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ቡድን ረቡዕ ሚያዚያ 22/2018 ዓ. ም. በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የጦር መሣሪያዎች መስፋፋትን አስመልክቶ በተካሄደው አሥራ አንደኛው ጉባኤ ላይ ወቅቱን እጅግ አሳሳቢ ሲል ገልጾ፥ ጂኦፖሊቲካዊ ውጥረት እየጨመረ መምጣት፣ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር መዳከም፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ጥቅም እና ሙከራን ጨምሮ ስለ ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክርክር  መነሳቱ ስጋትን እንደፈጠረ ገልጿል።

ከብዙ አገራት ዲፕሎማሲ ወደ ኋላ ማፈግፈግ

የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ንግግር በመጥቀስ፥ ከብዙ አገራት ዲፕሎማሲ መራቅ እንዳሳዘነው ገልጾ፥ በውይይት እና በስምምነት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲ በኃይል ላይ በተመሠረተ ዲፕሎማሲ እየተተካ መሆኑን በመጠቆም፥ በቅርብ ጊዜ በኔውክሌር ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ ደህንነትን የሚያስከብሩ የረጅም ጊዜ ደንቦች መሸርሸርን የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።

በኒውክሌር ውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሚና እየጨመረ መምጣቱ ልዩ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፥ ቅድስት መንበር እንዲህ ያሉ ሥርዓቶች በችግር ጊዜ የሰውን ልጅ ለማማከር የሚወስደውን ጊዜ እንደሚቀንሱ፣ የተሳሳቱ ስሌቶች አደጋን እንደሚጨምሩ፣ የሕይወት እና የሞት ምርጫዎች የሥነ-ምግባር ዋጋን በእጅጉ እንደሚቀንሱ ልዑካን ቡድኑ አስጠንቅቀዋል።

የመሣሪያ ትጥቅ መፍታት፣ የጦር መሣሪያ ምርት መቆም እና የኒውክሌር ኃይል ሰላማዊ አጠቃቀም

የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን የጦር መሣሪያ ምርት የማቆም ስምምነት አስፈላጊነትን እንደገና በማረጋገጥ፣ ሦስቱ መሠረታዊ ነጥቦች እነርሱም የጦር መሣሪያ ምርት ማገድ፣ እንዳይስፋፋ ማድረግ እና የኒውክሌር ኃይልን በሰላማዊ መንገድ መጠቀም ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግሯል።

የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ በስምምነት አንቀጽ ስድስት ላይ የተገለጸው ኒውክሌር የጦር መሣሪያን ለማስወገድ የሚደረገውን ድርድር ለመቀጠል አስገዳጅ ግዴታን እንደሚያስቀምጥ አፅንዖት ሰጥቶ፥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤቶች መሣሪያዎቻቸውን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ በሚጥሩበት ጊዜ እና የጥቃት ስልቶችን በሚያሰፉበት በዚህ ወቅት አስገዳጅ ስምምነነቱ እጅግ አስቸኳይ እንደሆነ አስታውቋል።

ልዑካን ቡድኑ በማከልም፥ “እንዲህ ያሉ አዝማሚያዎች ቀድሞውንም ስትራቴጂያዊ እና ሥነ-ምግባራዊ መንገድ  አጠራጣሪነትን የሚያጠናክሩ ናቸው” ሲል በማስረዳት፥ መከላከል ሲባል በሕግ እና በመተማመን ላይ ሳይሆን በኃይል ስጋት በሚደርስ የጋራ ተጋላጭነት ላይ የተመሠረተ የደህንነት አቀራረብን እንደሚያመላክት አስረድቷል።

በሰው ላይ ሊደርስ የሚችል ከፍተኛ መዘዝ

የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች አስከፊ ሰብዓዊ መዘዝን እንደሚያስከትል ያስታወሰው የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድኑ፥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ክልከላ ስምምነትን እንደሚደግፍ በድጋሚ ገልጾ፥ ይህም የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታትን የሚያስገድድ የሞራል እና የሕግ ማዕቀፍን እንደሚያጠናክር ገልጿል።

የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድኑ በረጅም መግለጫቸው፥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይስፋፋ በሚለው ላይ በማትኮር በመካከለኛው ምሥራቅ ጠንካራ የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጥበቃዎችን እንዲደርግ እና ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ ቀጠና እንዲቋቋም ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ የደህንነት መጓደል ዋና መንስኤዎችን በውይይት እና በኃላፊነት ሳይፈቱ ማረጋገጫው ብቻውን በቂ አለመሆኑን አስገንዝቧል።

"ሰላም በፍርሃት ላይ ሊሆን አይችልም"

ቅድስት መንበር የኒውክሌር ኃይልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን በተመለከተ፥ የሕክምና እና የግብርና ዘርፍን፣ የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢ ጥበቃን በመጥቀስ መንግሥታት ከግዴታቸው ጋር በሚስማማ መልኩ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ የማልማት መብታቸው እንዲረጋገጥላቸው ጠይቃለች። 

የቅድስት መንበር ልዑካን ቡድን በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የመሣሪያ ትጥቅ የሌለበት እና የጦር መሣሪያ ትጥቅን የሚያስፈታ ሰላም” እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥሪ በመጥቀስ፥ እውነተኛ ሰላም በፍርሃት ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደማይችል፥ በምትኩ በእምነት፣ በውይይት እና በጋራ ሰብዓዊነት እውቅና ላይ መገንባት እንዳለበት አሳስቧል።

 

01 May 2026, 14:39