ፈልግ

በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ የሚገኘው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነት ውይይት በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ የሚገኘው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነት ውይይት 

ቅድስት መንበር አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ብቸኛው እውነተኛ መንገድ የጦር መሳሪያ ቅነሳ እንደሆነ ገለጸች

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ ተወካይ በኒውዮርክ በተካሄደው 11ኛው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስምምነት ግምገማ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ተጨባጭ እና ተዓማኒነት ያለው እርምጃ የሚጠይቅ እጅግ አስፈላጊ ኃላፊነት” እንደሆነ አጉልተው በማሳየት የቅድስት መንበርን አቋም ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ፍትሃዊ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጦር መሳሪያ ቅነሳ ትልቁ እና ዋነኛው ተግባር” እንደሆነ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄንን ሰላም ለማግኘት እና አጠቃላይ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማስወገድ አስፈላጊው መንገድ በኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ (TPNW) ስምምነት በኩል የቀረበ መሆኑ ተነግሯል።

በዚህም ምክንያት ቅድስት መንበር ሁል ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አጠቃቀም የሚያስከትለው ድንበር እና ትውልድ የሚሻገር አስከፊ ሰብዓዊና አካባቢያዊ ውጤቶችን በመግለጽ እስካሁን ድረስ በዚህ ስምምነት ውስጥ ያልተካተቱ ሃገራት ስምምነቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪዋን እንደምታቀርብ ተገልጿል።

ይህ ጥሪ የቀረበው በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ ከሚያዝያ 19 እስከ ግንቦት 14 ድረስ እየተካሄደ በሚገኘው 11ኛው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስምምነት ግምገማ ወቅት ሚያዝያ 23 በነበረው ውይይት ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

ዘላቂ ሰላም
“በዓለም አቀፍ የደኅንነት መሠረት ላይ ያለው ጫና እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለዘላቂ ሰላም አስፈላጊ የሆኑትን ዋና ዋና ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው” ያለው የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ መግለጫ፥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ማስፈታት ዓላማው “በፍርሃት፣ በኃይል እና በጋራ ተጋላጭነት ላይ የተመሰረተውን፣ እንዲሁም ሰላምን ለማስፈን የተረጋጋ ወይም ዘላቂ መሠረት ማቅረብ የማይችለውን የጸጥታ ሞዴል ለማስቀረት እንደሆነም ጭምር ተመላክቷል።

ቅድስት መንበር “የኒውክሌር ጦር መሳሪያን የተመለከቱ ትርክቶች እንደ አዲስ መነሳታቸው፣ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች መዘመን እና መስፋፋት፣ እንዲሁም የመገደብ ደረጃዎችን በሚቀንስ መንገድ የዝግመተ ለውጥ አስተምህሮዎችን” የመሳሰሉት እሳቤዎች አሳሳቢ አዝማሚያዎች እንደሆኑ ያሳሰበች ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪ በጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና ትጥቅ መፍታት ላይ የተደረሱ ስምምነቶች መሸርሸር በዘላቂ መረጋጋት፣ ግልጽነት እና መተማመን ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ጠቁማለች።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ማስወገድ
በአጠቃላይ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መወገድ “የሩቅ ምኞት ሳይሆን ይበልጥ ፍትሃዊ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ተጨባጭ እና አስተማማኝ እርምጃዎችን የሚጠይቅ አስፈላጊ ኃላፊነት ነው” ሲል የገለጸው ቋሚ ተልዕኮው፥ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት ወደ ኒውክሌር ሲስተም ውስጥ መቀላቀላቸውን በማስመልከት ያላትን ስጋት በመግለጽ፥ ‘የኒውክሌር አደጋን የመቀነስ እና የማጥፋት እርምጃዎችን ማራመድ እንደሚያስፈልግ’ ጠቁማ፥ “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በደህንነት አስተምህሮዎች ውስጥ ያለውን ሚና” መገደብ እንደሚያስፈልግ እና “ግልጽነትን ማሳደግ እና የግንኙነት መስመሮችን ማጠናከር” አስፈላጊነትን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ በአፅንዖት አሳስባለች።

ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 191 አገራት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለሌሎች አገራት አሳልፎ ያለመስጠት ስምምነትን መፈረማቸው ይታወቃል።

04 May 2026, 14:54