ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከቬትናም ብፁዓን ጳጳሳት ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከቬትናም ብፁዓን ጳጳሳት ጋር   (@VATICAN MEDIA)

የቬትናም ጳጳሳት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቤተክርስቲያናቸው ቤተሰባዊ እንደሆነች ተናገሩ

የቬትናም ብፁዓን ጳጳሳት ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፥ የሹዋን ሎክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዶሚኒክ ንጉየን ቱአን ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ግንኙነቱ የወንድማማችነት እና ከልብ የመነጨ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

‘አድ ሊሚና’ ተብሎ የሚታወቀው የካቶሊክ ጳጳሳት በየአምስት ዓመቱ ወደ ሮም የሚያደረጉት ወቅታዊ እና ይፋዊ ጉብኝት ሲሆን፥ በዚህም ብፁዓን ጳጳሳቱ በቅድስት መንበር ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና ከቫቲካን ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ስለ ሀገረ ስብከታቸው ሁኔታ እና በቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩ፣ ብሎም በቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ መቃብር ሥፍራ ተገኝተው ጸሎት እንደሚያደርጉ ይታወቃል።

በዚህም ምክንያት የቬትናም ብፁዓን ጳጳሳት ወደ ሮም ተጉዘው ከአራት የአፍሪካ ሃገራት የ11 ቀናት ሐዋርያዊ ጉዞ በኋላ ወደ ቅድስት መንበር ከተመለሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ተገናኝተው ውይይት እንዳደረጉ የተነረገ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከኢኳቶሪያል ጊኒ በተመለሱ ማግስት ባደረጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ የቬትናም ብፁዓን ጳጳሳትን ማግኘታቸው ተገልጿል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ ከሐዋርያዊ መንበር ጋር በመተባበር ያደረጉት ይህ የአድ ሊሚና ጉብኝት ዓላማው እንደ ሐዋርያት ተተኪ ኃላፊነታቸውን እና ከጴጥሮስ ተተኪ ጋር ያላቸውን ተዋረዳዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ጳጳሳቱ በቆይታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ የመቃብር ስፍራ ተገኝተው ጸሎት እንደሚያደርሱ እና ይህ ጉብኝት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ አገልግሎት ውስጥም ቁልፍ ጊዜ ሆኖ እንደሚያገለግል፣ ብሎም ብፁዕነታቸው ከጳጳሳቱ ጋር ተገናኝተው የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተነግሯል።

የሹዋን ሎክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዶሚኒክ ስብሰባው በወንድማማችነት መንፈስ የሚደረግ እንደሆነ ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለ 11 ቀናት ወደ አፍሪካ ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ምንም እረፍት ሳያደርጉ በነጋታው ጊዜ ወስደው በሙሉ ልባቸው ከብፁዓን ጳጳሳቱ ጋር መገናኘታቸውን በአድናቆት ገልጸዋል።

ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ካቶሊኮች የሚገኙባት ቬትናም በእስያ አምስተኛው ትልቁ የካቶሊክ ማህበረሰብ መኖሪያ እንደሆነች የሚነገር ሲሆን፥ ብፁዕ አቡነ ዶሚኒክ እንደገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ጠንካራ እምነት” ስለሚታይባቸው በሀገሪቱ ስላሉት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከጳጳሳቱ በመስማታቸው እጅግ እንደተደሰቱ ገልጸው፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ቴክኖሎጂ በሚመራው ዓለም የቬትናም ቤተ ክርስቲያን እምነትን፣ ሰው ሰራሽ አስተሎት ወይም አርተፊሻል ኢንተለጀንስን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰራች እንደሆነ ገልጸው፥ እነዚህን የዘመናችን ፈተናዎችን ለመጋፈጥ “መሰባሰብ” እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቬትናም ብፁዓን ጳጳሳት የጉብኝታቸው አካል አድርገው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር መገናኘታቸውን አስመልክተው ብፁዕ አቡነ ዶሚኒክ እንደተናገሩት በመጀመሪያ ደረጃ ብፁዕነታቸው ከረጅሙ የአፍሪካ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በኋላ ድካም ቢኖርባቸውም ጊዜ ወስደው እነሱን በማየታቸው እና ስለ ቬትናም ቤተክርስቲያን ከእነሱ በመስማታቸው በጣም ደስተኛ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ከብፁዓን ጳጳሳቱ ጋር የተገናኙበት መንገድ በጣም ወንድማማቻዊ እንደነበር ያስታወሱት ጳጳሱ፥ ብፁዕነታቸው በእውነትም የቅዱስ ጴጥሮስ ምትክ እንደሆኑ እና ብፁዓን ጳጳሳቱም የሐዋርያት ተተኪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጉብኝቱ ቤተሰባዊ እንደነበር እና በቤተክርስቲያን ውስጥ አንድነትን እና ህብረትን ለመፍጠር ሁሉም ጳጳሳት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ከቅድስት መንበር እና ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጋር ኅብረት እንዳላቸው ከልብ እንደሚሰማቸው እና የቬትናም ቤተ ክርስቲያን ቤተሰባዊ እንደሆነች ብሎም በእነሱ ባህል ቤተሰብ በጣም ጠንካራ መሰረት መሆኑን እና ቤተክርስቲያንም በእግዚአብሔር ቸርነት እና በሰማዕቶች ደም መባረኳን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በቬትናም ቤተክርስቲያን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል የተጠየቁት ብፁዕ አቡነ ዶሚኒክ፥ እሳቸው እንደሚያስቡት በቤተክርስቲያን ውስጥ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያትን እና ምዕመናንን ጨምሮ የሁሉም ሰው አስተዋፅኦ እና አንድነት ሁልጊዜ እንደሚያስፈልግ የገለጹ ሲሆን፥ በሃገሪቷ ውስጥ የምትገኘው ቤተክርስቲያን በጠንካራ እምነቷ እንደምትታወቅ አስታውሰው፥ ነገር ግን እንደማንኛውም ሰው ሁሉንም ፈተናዎች እየተጋፈጡ እንደሚገኝ፥ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ማህበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ትልቅ ተግዳሮት እንዳለ ጠቅሰው፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት አንድ መሆን እንደሚገባ እና በእግዚአብሔር ጸጋ ይህንን ፈተና በእምነት እና በተስፋመንገድ መጋፈጥ እንደሚችሉ በማስረዳት አጠቃለዋል።

27 Apr 2026, 14:30