የቤተሰብ ሕይወት የቤተሰብ ሕይወት  

ቫቲካን በቤተሰብ ውስጥ ስለ ሁሉ አቀፍ ሥነ-ምህዳር የሚያወሳ ሠነድ ይፋ አደረገ

በቅድስት መንበር ሁሉ አቀፍ የሰው ልጅ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ “በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር” በሚል ርዕሥ፥ ለፍጥረት እና ለሰው ልጅ ሕይወት ከሚደረግ እንክብካቤ ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን የያዘ ሠነድ ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቫቲካን “በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር” በሚል ርዕሥ በቤተሰብ ውስጥ ለፍጥረት እና ለሰው ልጅ ሕይወት በሚደረግ እንክብካቤ ላይ ያተኮረ ሠነድ አሳትሟል።

“በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር” በሚል ርዕሥ ሰኞ ሚያዝያ 19/2018 ዓ. ም. ይፋ የሆነው ጽሑፉ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የድሆችን እና የምድርን ጩኸት በማዳመጥ ተጨባጭ ምላሽ እንዲሰጥ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የታሰበ ነው ሲል” የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ሠነዱ የታተመው “የፍቅር ደስታ” እና “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከሚሉት የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ በኋላ ከወጡት የሐዋርያዊ ሠነዶች የምስጋና መርሆች እና ትምህርቶች በተወሰዱ ምክረ-ሃሳቦች መሆኑ ታውቋል።

አዲሱ ሠነዱ የተዘጋጀው በቅድስት መንበር ሁሉ አቀፍ የሰው ልጅ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በጋራ ባደረጉት ጥረት ሲሆን፥ የሃይማኖት ሊቃውንት፣ አማካሪዎች እና ባለትዳሮች ባደረጉት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሆነ ታውቋል።

ቤተሰቦች ኅብረተሰቡ የሚያድግበት መሬት ናቸው

“የቤተሰብ እሴቶች መላው ኅብረተሰብ የሚያድግበት ፍሬያማ አፈር ናቸው፤ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እና ሰዎችን በሙሉ በአግባቡ ለመንከባከብ ቤተሰቦች ሞዴል መሆን አለባቸው” ሲሉ የሁለቱ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሃላፊዎች ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ እና ብጹዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል ጽፈዋል።

“በርካታ ቤተሰቦች የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እና ሌሎችን በመንከባከብ ረገድ በትኩረት ይሠራሉ፣ አእምሯቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ ላይ ያተኮረ ነው፤ የቤተሰብ እሴቶች የጋራ ቤታችንን እና ጎረቤቶቻችንን ለመንከባከብ ወጥነት ያላቸው እና መሠረታዊ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

“የቤተሰብ እሴቶች የትኞቹ ናቸው? የቤተሰብ አባላት ራስ ወዳድነት በሌለበት፣ ትዕግስትን፣ ቁርጠኝነትን፣ ግልጽነትን እና የሕይወት ጥበቃን በመማር፣ በመበልጸግ፣ እርስ በርስ በመተሳሰር፣ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ትውልዶችን በማገናኘት እውቀትን እና ወጎችን ማስተላለፍ ይችላሉ” ብለዋል።

መመሪያዎች እና አስተያየቶች

ሠነዱ ለቤተሰቦች፣ ለቤተ ክርስቲያን ቡድኖች እና ለግለሰቦች ወቅታዊ የአካባቢ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና የእያንዳንዱን ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት ለማበረታታት የሚረዱ መመሪያዎችን ይሰጣል።

የሠነዱ የመጀመሪያ ክፍል በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ እጅግ ግልጽ በሆኑ ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ መሠረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ሲሆን፥ የሠነዱ ዋና ልብ የሆነው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ መልዕክት ዓላማዎችን የሚያንፀባርቁ የሰባት ምዕራፎች ጭብጦችን መያዙ ተመልክቷል።

እነዚህም፥ የምድርን ጩኸት ማዳመጥ፣ የድሆችን እና የተቸገሩ ሰዎችን ጩኸት ማዳመጥ፣ ሥነ-ምህዳራዊ ምጣኔ ሃብትን መቀበል እና ማስፋፋት፣ ሥነ-ምህዳራዊ የአኗኗር ዘይቤዎችን መቀበል፣ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳራዊ እና ትምህርት፣ በቤተሰብ ውስጥ ሥነ-ምህዳራዊ መንፈሳዊነት እና በማኅበረሰብ ሕይወት የሚሳተፉ ቤተሰቦች” የሚሉትን ያካትታሉ።

እያንዳንዱ ምዕራፍ አራት ክፍሎች የያዘ ሲሆን፥ እነርሱም የርዕሡ ማብራሪያ፣ የርዕሱ አንድምታ፣ ለአስተንትኖ እና ለውይይት የቀረቡ ጥያቄዎችን እና ዕቅድ ዝርዝሮችን የያዘ እንደሆነ ተመልክቷል።

መግለጫው አክሎም፥ ሠነዱ ለቤተሰቦች የታሰበ ቢሆንም ለሁሉም ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በማስረዳት፥ ለፍጥረት የሚደረግ እንክብካቤን እና የሰው ልጅ ክብርን ማስፋፋት ሁሉንም የሚነኩ ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸውን ከማስገንዘብ በተጨማሪ፥ ቤተሰቦች የኅብረተሰቡ ዋና አካል በመሆናቸው የዚህ ጥልቅ የባሕል ለውጥ አንቀሳቃሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

Integral Ecology in the Life of the Family” የሚለውን ሠነድ በሁለቱም ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ኦፊሴላዊ ድረ-ገጾች ላይ በ አምስት ቋንቋዎች በነፃ ያግኙ።

29 Apr 2026, 17:01