የአሜሪካ እና የኢራን ውይይት በፓኪስታን እንደሚቀጥል ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ውይይት በሳምንቱ መጨረሻ በፓኪስታን ይቀጥላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የዩናይትድ ስቴትስ የልዑካን ቡድን ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ኢስላማባድ የገቡ ሲሆን፥ ነገር ግን ከዚህን ቀደም በነበሩት ውይይቶች ወቅት መሪ ተደራዳሪ የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንደማይሳተፉ ተነግሯል።
ሆኖም ግን ቀድሞውኑ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ የነበሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካውያን ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ውይይት እንደማይደረግ ገልጸዋል።
የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች ከዚህ ቀደም በፓኪስታን ኢስላማባድ ለሁለተኛ ዙር የሰላም ውይይት ቢጠሩም የኢራን ልዑካን ሳይመጡ በመቅረታቸው ድርድሩ መቋረጡ ይታወሳል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደማይቸኩሉ የገለጹ ሲሆን፥ ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ መናር እና አንዳንድ ሁኔታዎች ድርድሩ በፍጥነት እንዲካሄድ የሚደረገው ግፊት እየጨመረ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለሥልጣናቱ ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል በጊዜ ማለፍ ካልቻሉ በዓለም ድሃ ሃገራት ላይ ከፍተኛ የምግብ ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በተያያዘ ዜና በሊባኖስ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ ሲቪሎች ከተፈቀደላቸው የድንበር መስመሮች እንዳያልፉ በማሳሰብ ሌላ ማስጠንቀቂያ ማውጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ እስራኤል በ10 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የጸጥታ ቀጠና እንደሚኖር ማስታወቋን ተከትሎ በተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ወታደሮቿ ቦታቸውን ይዘው እንደሚቆዩ እና “ቢጫ መስመር” የተሰኘ የፀጥታ ድንበር እንደማይነሳ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።