ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በታላቁ የአልጀርስ መስጊድ ከኢማም መሐመድ ማሙን አል ቃሲሚ ጋር ተገንኝተው ሰላምታ ሲለዋወጡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በታላቁ የአልጀርስ መስጊድ ከኢማም መሐመድ ማሙን አል ቃሲሚ ጋር ተገንኝተው ሰላምታ ሲለዋወጡ  (@Vatican Media)

ብፁዕ ካርዲናል ኮቫካድ የር.ሊ.ጳ. ሊዮ የአፍሪካ ጉብኝት ሀይማኖቶች ወደ ሰላም የሚያመሩ ልዩ መንገዶች መሆናቸውን ያሳያሉ አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ አንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ መጠናቀቁን ተከትሎ በቫቲካን በተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደርገውን ውይይት በበላይነት የሚቆጣጠረው የቅድስት መንበር ዋና ጽህፈት ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ ኮቫካድ ብፁዕነታቸው የሃይማኖት ተቋማት ፍትህን፣ ማኅበራዊ መረጋጋትን እና በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ አብሮ መኖርን ለመገንባት ያላችውን ሚና አስመልክቶ ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ላይ ያላቸውን አመለካከት አጋርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአራት የአፍሪካ ሃገራት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት ያከናወኗቸው ሃይማኖታዊ ጉዳዮች በተለይ በአልጄሪያ እና በካሜሩን ውስጥ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው፥ ከዚህም ባሻገር በአንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ብፁዕነታቸው ለባለሥልጣናት እና ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያደረጉትም ንግግር ጭምር ትልቅ ትርጉም እንደነበረው በቅድስት መንበር የኃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ አመላክተዋል።

በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ወጥ የሆነ የውይይት መድረክ ወደ ሰላም፣ ዕርቅ እና ማህበራዊ መረጋጋት ለመምጣት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ እነዚህ ተምሳሌታዊ ምልክቶች እና ቃላቶች በተመሳሳይ ሥነ-መለኮታዊ እና ሃዋሪያዊ አተያይ ውስጥ የሚሰባሰቡበት ጥረቶች ለየብቻ ከመጓዝ ይልቅ አንድ ላይ ሲደመሩ ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የመጀመሪያው የአልጄሪያ ጉዞዋቸው ገና ከጅምሩ ወደ ግንኙነት ግንባታ እና ዕርቅ በማምራት ራሱን እንደገለጠ ያስታወሱት ካርዲናሉ፥ ብፁዕነታቸው በተመሳሳይ ድምጽ ለመቀጠል እና ማስተላለፍ የምንፈልገውን ተመሳሳይ መልዕክት ለማስተላለፍ ይህ እጅግ ጠቃሚ አጋጣሚ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ ስምምነትን እና በሁሉም ህዝቦች ዘንድ መከባበርን ለማጎልበት፣ ቅዱስ አውገስጢኒዮስን በመጥቀስ “በሃይማኖታዊ ውይይቶች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ድልድይ” እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአልጀርስ ለሲቪል ባለ ሥልጣናት ባደረጉት ንግግር “በሰማይ የሚኖረው አባታችን አንድ ስለሆነ ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” በማለት ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነትን የንግግራቸው ማዕከል አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ፥ ይህም እምነት ፍትሕን፣ ኅብረትንና ሰላምን ለማስቀጠል የሚያስችል የአንድነት መርህ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በተለይ ብፁዕነታቸው “እያንዳንዱ የሰው ልጅ ክብር እንደሚገባው” በድጋሚ ያረጋገጡበት ታላቁን መስጊድ በጎበኙበት ወቅት ይህ አካሄድ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የጠቆሙት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ “እርስ በርስ መከባበርን፣ ተስማምተን መኖርን እና ሰላማዊ የሆነ ዓለም መገንባትን መማር እንችላለን” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

በክብር መጽሐፍ ውስጥ ባሰፈሩት መልዕክታቸው መላው የአልጄሪያ ህዝብ እንዲሁም መላው የሰው ልጅ በልዑል እግዚያብሔር ምህረት በሰላም እና በነጻነት እንዲኖር መጸለያቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በዚህም ይህንን ዓለም አቀፋዊ ራዕይ በተሳካ ሁኔታ ማጠቃለላቸውን አመላክተዋል።

ውይይት በተጨባጭ እና በዕለት ተዕለት መልኩ በሚገለጽበት የአፍሪካ እመቤታችን ባዚሊካ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመግለጫቸው እንደገለጹት እምነት “ከሌላው የሚነጥለን ሳይሆን ግልጽ እንድንሆን እና አንድ ላይ የሚያስተሳስረን፣ ግራ መጋባትን የሚፈጥርብን ሳይሆን አንድ የሚያደርገን፣ እንዲሁም ያለ ልዩነት የሚያቀራርበን ነገር መሆኑን ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም የቅዱስ አውጎስጢናዊያን አመለካከት ሃይማኖታዊ ጉዞውን በጥልቅ መንፈሳዊ እይታ ላይ በሰፈረባት አናባ ከተማ እግዚአብሔርን መፈለግ ከሰላም ግንባታ እና ከበጎ አድራጎት ጋር በማያያዝ በአንድ አምላክ ማመን… ሰዎችን ፍፁም በሆነ ፍትህ ሁሉንም ሰው ወደ በጎ አድራጎት ሥራ በመጋበዝ አንድ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በካሜሩን በነበራቸው ቆይታ የአንግሊፎን ቀውስ ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት ባልተሸጋገረበት አውድ ውስጥ፥ የሃይማኖት ተቋማት ‘በሃማኖታዊ አክራሪነት መርዝ’ ካልተዛቡ ሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን ትልቅ ሚና በግልጽ መጥቀሳቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ አክለውም ብፁዕነታቸው ለሲቪል ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግር ሁሉም ሰው ግጭትን በመከላከል ረገድ የሃገራት እና የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ሃላፊነትን በማጉላት፥ የጦር መሳሪያ የሌለበት ሰላምን ለማስፈን የአመፅ እና የጦርነት አመክንዮን ውድቅ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ወቅት በጣም ወሳኙ ጊዜ ባሜንዳ ከተማ የተደረገው የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የባህላዊ ሃይማኖት መሪዎች ስለ ወንድማማችነት ተጨባጭ ምስክርነት የሰጡበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው፥ የመስጊዱ ኢማም በወቅቱ እንደተናገሩት፣ “ይህ ቀውስ ወደ ሃይማኖታዊ ጦርነት ስላልተሸጋገረ አምላክን እንደሚያመሰግኑ” ገልጸው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በበኩላቸው ‘የሰላም ንቅናቄው’ “ለዓለም ሁሉ አርአያ” እንደሆነ መናገራቸውን እና ለራቸው ግላዊ ፍላጎት ሲሉ “ሃይማኖትን መጠቀሚያ” የሚያደርጉ አካላትን ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

ይህ መርሃ ግብር በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይት ከጋራ የስቃይ ታሪክ የሚነሳበትን መንገድ እና ወደ እርቅ የሚወስዱ መንገዶችን ማሳየቱን የገለጹት ካርዲናሉ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሙስሊም ተወካዮች እና ከተለያዩ ብፁዓን ጳጳሳት ጋር ባደረጉት ውይይት የሃይማኖት ማህበረሰቦችን ውስጣዊ ልዩነት በመገንዘብ እና እውነተኛ መሠረተ ልማትን ለማጎልበት ሰላምን ለመገንባት የጋራ ሃላፊነት እና ተጨባጭ ውይይት አስፈላጊነት ላይ አጥብቀው መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በአንጎላ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ባደረጉት ንግግር ሰላምን ለመገንባት የሃይማኖታዊ ማህበረሰቦችን ውስጣዊ ልዩነት የሚገነዘብ እና ትክክለኛ አመንክዮን ማስተዋወቅ የሚችል የጋራ ሃላፊነት እና ተጨባጭ ውይይት አስፈላጊነት ላይ በማተኮር መናገራቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አክለውም አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ አንዳንድ ሁኔታዎችን እና ተለዋዋጭ የሆኑ ግጭቶችን እንዲሁም የጠላትነት ስሜትን በአስቸኳይ ማሸነፍ እንዳለባት መናገራቸውን የጠቆሙት ካርዲናሉ፥ ይሄንንም ለማሳካት ውይይት የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ በነበራቸው ቆይታ “በእብሪት በተሞላው ዓለም ውስጥ ሰዎች ፍትህን እንደሚራቡ እና እንደሚጠሙ” በመግለጽ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ጥሪ ማስተጋባታቸውን አስታውሰው፥ እኛ በአሁኑ ዘመን ያለነው ደግሞ የኢኮኖሚ መድልዎን እና ኢፍትሃዊነትን መቃወም እንደሚገባ መምከራቸውን አስታውሰዋል።

በጠቅላላው ሲታይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ትሩፋት በማስታወስ፣ “ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን” እና “ለሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ትክክለኛ አክብሮት” የመስጠት ቁርጠኝነትን ያነሱ ሲሆን፥ ሃዋሪያዊ ጉብኝታቸው በተለያዩ ጉዳዮች የታጀበ መሆኑን በማመላከት፥ ከእነዚህም ውስጥ ወንድማማችነትን አብሮ የመኖር መሰረት ማድረግ፣ ሃይማኖትን እንደ መሳሪያ መጠቀምን ማውገዝ እና የሃይማኖት መሪዎች ግጭቶችን በማስታረቅ ረገድ የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ በመጨረሻም በዚህ አተያይ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የተከሰቱት ተሞክሮዎች የተለዩ ክስተቶች ሳይሆኑ በወቅታዊው ዓለም በሕዝቦች መካከል ሰላምን፣ ፍትሕን እና የተረጋጋ አብሮ መኖርን ለማስቀጠል የሚያስችል የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይትን ለማበረታታት እንደ አንድ ወጥ እና ተጨባጭ ምክረ ሃሳብ እንደሚታዩ በመግለጽ አጠቃለዋል።

24 Apr 2026, 14:51