ቫቲካን ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሥነ ምግባርን የሚመለከት ትምህርታዊ ጉባኤ ማዘጋጀቷ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“የተትረፈረፈ ዘዴዎች እና የፍጻሜዎች ግራ መጋባት” በማለት አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት የተናገረው ቃላት አሁን የምንገኝበት ዓለም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ምክንያት የገጠመውን ተግዳሮት እና በዚህም የተቀረፀውን ዓለም ቅጽበታዊ እይታ የሚያሳይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በችግሩ ላይ ያሉት ፍላጎቶች በርካታ ይሁኑ እንጂ “ገለልተኛ” አይደሉም ተብሏል።
በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ ምንም ዓይነት ወታደራዊም ሆነ የንግድ ዓላማ የሌላት ቅድስት መንበር ከአመሰራረት ደረጃቸው ጀምሮ ሥነ ምግባራዊ የሆኑ ሥርዓቶችን ማዳበር የሚያስችል ዓለም አቀፍ አስተዳደርን በማስተዋወቅ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወት ትችላለች ተብሏል።
“የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አቅም እና ተግዳሮቶች” በሚል ጭብጥ የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በሮም ውስጥ በሚገኘው ‘ሳሎን ሳን ፒዮ 10ኛ’ አዳራሽ ውስጥ በቫቲካን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የሰራተኞች ቢሮ (ULSA) በተዘጋጀው ትምህርታዊ ጉባኤ ወቅት ትኩረት ከተደረገባቸው አንዳንድ ጭብጦች መካከል ቅድስት መንበር ሥነ ምግባራዊ የሆኑ ሥርዓቶችን ማዳበር የሚያስችል ዓለም አቀፍ አስተዳደርን በማስተዋወቅ ረገድ ያላት አስተዋጽዖ መነሳታቸው ተገልጿል።
ዝግጅቱ የተከፈተው የሐዋርያዊ መንበር የሰራተኞች ቢሮ ዳይሬክተር በሆኑት ፕሮፌሰር ፓስኳል ፓሳላኳ ሲሆን፥ ፕሮፌሰሩ የተነሳሽነቱ ፕሬዚዳንት በሆኑት ሞንሲኞር ማርኮ ስፕሪዚ በኩል ስለጉባኤው የሰሙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ራሳቸው ይሄንን ተነሳሽነት “እንደሚያደንቁ እና እንደሚያበረታቱ” በመግለጽ፥ ብፁዕነታቸው “በዚህ በጣም ጠቃሚ እና ውስብስብ መስክ ላይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ” እንዲኖር ያላቸውን ተስፋ መግለጻቸው ተነግሯል።
ውይይቱን የመሩት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ኤዲቶሪያል ዳይሬክተር በሆኑት አሌሳንድሮ ጊሶቲ ሲሆን፥ በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት በቅድስት መንበር የባህል እና የትምህርት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ፖል ቲጌ፣ በጎርጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በሉዊስ ጊዶ ካርሊ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍራንቺስካዊው ካህን አባ ፓኦሎ ቤናንቲ እንዲሁም ሮም በሚገኘው ባዮ-ሜዲኮ ዩኒቨርሲቲ የኢንተለጀንት ሲስተምስ ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኮራዶ ገስቶዚ እንደሆኑ ተገልጿል።
እ.አ.አ. በ 2022 ‘ቻትጂፒቲ’ በተሰኘው መተግበሪያ ላይ የተስፋፋውን የአጠቃቀም ሂደት የሚያስከትለውን መዘዝ አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ቲጌ በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል ቪዩሲኤ VUCA ማለትም ተለዋዋጭነት፣ አለመተማመን፣ ውስብስብነት እና አሻሚነት የሚሉትን ቃላት የተጠቀሙ ሲሆን፥ በዚህ ረገድ በቅርቡ የተከሰቱ ለውጦችን እና የተሻለ ሥነ ምግባራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን የማበረታታት ዓላማ ያለው በአሜሪካ የተመሠረተውን የአንትሮፒክ ኩባንያን ጉዳይ በመጥቀስ፥ ኩባንያው ወታደራዊ እና የቁጥጥር ሂደቶችን በሚመለከት ስነ-ምግባራዊ ዝግጁነቱን እንዲያሳርፍ የመንግስት ግፊት እንዲኖር ያለውን ፍላጎት አመላክተዋል።
ብፁዕ አቡነ ቲጌ ከዚህም ባሻገር የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እድገት በገለልተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ ሳይሆን “ከጂኦፖለቲካዊ ፉክክር፣ ከንግድ ጫናዎች እና የግል ምኞቶች” ጋር የተቆራኘ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፥ እንዲህ ያሉ ውስብስብ ነገሮች በሚያጋጥምበት ወቅት በአሁኑ ጊዜ ለሁሉም የሰው ልጆች በጣም የሚያስፈልገውን “ልባዊ ጥበብን እንዲሁም አጠቃላዩን እና የተለያዩ ክፍሎቹን የማዋሃድ ችሎታን” ስለሚገልጸው ‘አንቲኳ ኤት ኖቫ’ የተሰኘውን ሰነድ ማየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያን በበኩሏ “የሞራል ስልጣን” እና ብቃት ያላቸውን የውይይት ተካፋዮችን የማሰባሰብ ችሎታ እንዳላት የጠቆሙት ጳጳሱ፣ በዚህም ቤተክርስቲያኒቷ የሰውሰራሽ አስተውሎት እድገትን በመምራት ረገድ ጠንካራ አጋር እንደምትሆን አመልክተው፥ የጣልቃ ገብነት ጭብጦችን አንድ ላይ በማጠቃለል ትምህርታዊ ጉባኤው በቤተ ክህነቱ ማህበረሰብ በኩል ያለውን “ቁርጠኝነት” እንደሚወክል አስምረውበታል።
አባ ቤናንቲ በበኩላቸው ያቀረቡት የመወያያ ሃሳብ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የስነ-ምግባር ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በእንደዚህ ዓይነት አሰራሮች ውስጥ የተካተቱትን "ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችን" የሚጠይቅ አዲስ “የቴክኖሎጂ ስነምግባር” ያቀረቡ ሲሆን፥ ‘እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ ቅርስ በማህበራዊ አውድ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ የኃይል ውቅር እና ሥርዓትን ይከተላል’ ሲሉ ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮሚቴ ውስጥ ብቸኛው ጣሊያናዊ አባል የሆኑት አባ ቤናንቲ በንግግራቸው ወቅት ይህ አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰው፥ ከቅድስት መንበር እስከ የተባበሩት መንግስታት ድረስ ስለ ጉዳዩ ተነስቶ ‘በተለያዩ ጠረጴዛዎች’ ላይ ለውይይት መቅረቡን ጠቁመው፥ እነዚህ “የኃይል ውቅሮች” ወይም አጠቃቀሞች በንግድ ስምምነቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩና ይህ ተለዋዋጭነት በመረጃ መስክም እንደሚንጸባረቅ የገለጹ ሲሆን፥ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን የአንድ ጽሁፍ እይታ የግድ በጥራት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን፥ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አልጎሪዝም በድረ-ገጾች ላይ በሚሰጠው አቋም ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስ “ይህ የኃይል ጣልቃ ገብነት ነው” በማለት አጠቃለዋል።
ፕሮፌሰር ጉስቶዚ በበኩላቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስፈላጊ አካላት ውስጥ አንዱ በሆነው የአርጎሪዝም ተፈጥሮ ላይ በማተኮር፥ አልጎሪዝም እና በእሱ ላይ ተመስርተው ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ጋር የተያያዙ ወሳኝ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል የአድሎአዊነት ችግር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ አልጎሪዝም ወይም ስልተ ቀመሮች አንዳንድ ጊዜ ባለማወቅም ይሁን ሆን ተብሎ ጭፍን ጥላቻን እንደሚያካትት እና በዚህም ውጤቱን የሚያዛባ ወይም ኢፍትሃዊ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
ከዚህ አንጻር በመረጃ ግብአት በኩል አልጎሪዝም የሚዘጋጅበት ምዕራፍን ያካተተ ስልጠና ወሳኝ አስፈላጊነትን ጠቁመው፥ መረጃው ያልተሟላ ወይም የተዛባ ከሆነ ውጤቶቹ የተሳሳቱ ወይም አድሎአዊ መሆናቸው የማይቀር እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል።