ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በጦርነቶች ለተበታተነው ዓለም ሰላም እንደሚያስፈልግ ባሳሰቡበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በጦርነቶች ለተበታተነው ዓለም ሰላም እንደሚያስፈልግ ባሳሰቡበት ወቅት  (ANSA)

ቅዱስ ሲኖዶስ በዲጂታሉ ዓለም ያለውን ተልዕኮ በማስመልከት ሪፖርት ማውጣቱ ተገለጸ

የቅዱስ ሲኖዶስ የጥናት ቡድን ሦስት በመጨረሻው ሪፖርቱ፥ ቤተ ክርስቲያን ዲጂታል ዘዴን ለወንጌል አገልግሎት፣ ለውይይት እና ሐዋርያዊ ድጋፍን ለመስጠት ወሳኝ ቦታ አድርጋ ማሳተፍ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የቤተ ክርስቲያን በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ መገኘት የኅብረት ምልክት እና የተስፋ ምስክር ሊሆን ከመቻሉ በተጨማሪ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ሊያንጸባርቅ ይችላል” ሲል የገለጸው የሲኖዶስ የጥናት ቡድኑ ዲጂታሉ ዘርፍ በዛሬው ዓለም ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አስፈላጊ ቦታ እየሆነ መምጣቱን አፅንዖት ሰጥቷል።

“በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ያለው ተልዕኮ” በሚል ርዕሥ በጥናት ቡድን 3 የቀረበው አስተያየት በ16ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ አማካይነት በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኩል በቀረቡ ኅብረት፣ ተሳትፎ እና ተልዕኮ በሚሉ የሲኖዶሱ ሂደት አካል ሆኖ መዘጋጀቱ ታውቋል።

ሠነዱ እንዳስታወቀው ዲጂታሉ ዓለም የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ስብስብ ብቻ ሳይሆን የራሱ ቋንቋ፣ የለውጥ ኃይል እና ግንኙነቶችን የመፍጠር መንገዶች ያሉት የባህል ቦታ መሆኑን ይገልጻል። በዚህ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን እንድታውጅ የተጠራችበትን አዲስ ሚስዮናዊ መስክን ይወክላል።

የዲጂታል ዘመን ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርነት

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የቅርብ ጊዜ አስተንትኖዎች የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ ክርስቲያኖች በማኅበራዊ አውታረ መረቦች እና በበይነ መረብ ላይ ክርስቲያናዊ ተስፋን ለሌሎች ለማካፈል ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱ አበረታቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስን ስጦታ ለዓለም የሚያደርሱ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት በማኅበራዊ አውታረ መረቦች ላይ ለሚያገኟቸው ሰዎች ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሪፖርቱ አክሎም “ዲጂታሉ ዓለም ከዕለት ተዕለት ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር በተለይም ከወጣቶች ጋር እየተቆራኘ መሄዱ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ተሳትፎ እና ለወንጌል ምስክርነት ወሳኝ ቦታ እንዲሆን ያደርገዋል” ሲል አመልክቷል።

በውይይቱ ወቅት ቡድኑ “ዲጂታል የመገናኛ መሣሪያዎች በተለይም ለብዙ ሰዎች ዋና የተሳትፎ መንገድ በሆነበት ዓለም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ወይም ተጨማሪ መሣሪያ አድርጎ ከማየት ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለተልዕኮዋ አስፈላጊ እንደሆነ እውቅና መስጠት አለባት” ሲል አሳስቦ፥ “በይነ መረብን የመጠቀም ዘዴ ብዙ ሰዎች ስለ ወንጌል እና እግዚአብሔርን ስለማግኘት ጨምሮ ሁሉም ጠቃሚ ነገሮችን ለማግኘት የሚሄዱበት መንፈሳዊ የመሰብሰቢያ ሥፍራ አድርገው ተቀብለውታል” ሲል ገልጿል።

አምስት አስፈላጊ ጭብጦች

የመጨረሻው ሠነድ፥ ምን ሰምተናል? ምን ማለት ነው? እና ምንን እንመክራለን? የሚሉ ሦስት መሪ ጥያቄዎች አቅርቦ፥ በእነዚህ ሦስት ጥያቄዎች አምስቱ አስፈላጊ ጭብጦችን አውጥቷል።

አንደኛ፥ ዲጂታሉን ዓለም ለመለማመድ የሚያስፈልጉ የዘመናዊ መሣሪያዎች ስብስብ ብቻ ሳይሆን ባህልም ጭምር እንደሆነ፤

በሁለተኛ፥ ዲጂታል ተሳትፎ ድምፃቸው የማይሰማባቸውን ሰዎች ድምጽ ማዳመጥ፣ ማገዝ እና ከፍ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ተልዕኮ መገለጫ እንደሆነ፤

ሦስተኛ፥ ይህ ዲጂታል ባህል ለማንኛውም ባህላዊ አገልግሎት የምናቀርበውን ተመሳሳይ ዓላማ፣ ስልጠና እና የሚስዮናዊነት መንፈስ እንደሚያስፈልገው፤

አራተኛ፥ ዲጂታል ተሳትፎ በተፈጥሮ የሲኖዶሳዊነት መርሆችን፣ ማዳመጥን፣ ተሳትፎን እና የጋራ ኃላፊነትን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያዳብር መረዳት፤

አምስተኛ፥ በተመሳሳይም ዲጂታሉ ዓለም ከፍተኛ ፈተናዎችን እና ከባድ አደጋዎችን እንደሚያስከትል፣ ማግለል እና ማታለል በሚችሉ ስልተ ቀመሮች የተቀረጸ መሆኑን ማውቅ የሚሉት ናቸው። እነዚህን ክስተቶች ለመረዳት የሚደረገው ጥረት በተለይም ዲጂታል ሚስዮናዊነት ብቅ እያለ ማደግ መቀጠሉ ታውቋል።

ዛሬም በማደግ ላይ ያለ ተልዕኮ

የጥናት ቡድኑ የሚያበቃው በቅድስት መንበር፣ በጳጳሳት ጉባኤዎች እና በሀገረ ስብከቶች ደረጃዎች ላይ በተቀመጡት ሃሳቦች ሲሆን፥ ይህንን የቤተክርስቲያን ተልዕኮ በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ እርምጃዎችን በመጠቆም፥ “እንደ አዲስ የሚስዮናዊነት በዲጂታል አካባቢ ያለው ተልዕኮ በሂደት ላይ ያለ ጉዞ ነው” ሲል ሪፖርቱ ገልጿል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉ በሄዱ ቁጥር እንደ ዲጂታል ተልዕኮ፣ የበይነ መረብ ላይ ሲኖዶሳዊነት እና ዲጂታል እገዛ የመሳሰሉ ፅንሰ ሃሳቦችን ለመረዳት ተጨማሪ ሥነ-መለኮታዊ፣ ሐዋርያዊ እና ቀኖናዊ አስተንትኖ አስፈላጊ እንደሚሆን ታውቋል።

በመጨረሻም ሠነዱ የቤተ ክርስቲያን በዲጂታል ዓለም ውስጥ መገኘት በፍጥነት በሚለዋወጥ የባህል ገጽታ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት የሚያንፀባርቅ የኅብረት እና የተስፋ ምልክት ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል።

 

18 Mar 2026, 15:40